የኢትዮጵያ ባህል ሕክምና ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ባህል ሕክምና ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው

አዲስ አበባ 13/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ባህል ሕክምና ትኩረት ከተሰጠው ለማህበረሰቡ ከሚሰጠው የጤና አገልግሎት ባሻገር ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ የባህል ሕክምና አዋቂዎች ማህበር አስታወቀ፡፡
የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሎሬት አለሙ መኮንን ለኢዜአ እንደተቆሙት ኢትዮጵያ በባህል መድኃኒት የረጅም ጊዜ ታሪክ አላት።
ይሁንና ባለፉት ዘመናት ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን ዘርፉን በተሻለ ማሳደግም ሆነ ህዝብን በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ማድርግ አልተቻለም።፡
ዛሬ የሩቅ ምስራቅ አገራት ለባህላዊ መድኃኒቶች በሰጡት ትኩረት በዓለም አቀፍ ደረጀ እውቅና ለማግኘት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡
እንደ ህንድ፣ ቻይናና ኢንዶኔዥያ ያሉ አገራት በባህላዊ ሕክምናቸውየህዝባቸውንጤናከመጠበቅ
ባለፈ ለአገራቸው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ላይ ይገኛሉ፡፡
"የኢትዮጵያ የባህል ህክምና ረጅም ዕድሜን ያስቆጠረ ነው" ያሉት ሎሬት አለሙ፣ ለእዚህም የባህል መድኃኒት አዋቂዎች በአድዋ ጦርነት ከዘመተው ሠራዊት ጎን በመቆም የህክምና አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከረጅም ታሪኩ በመነሳት ኢትዮጵያዊያን በተለይ ወላጆች የባህል ህክምናዎችን በቤት ውስጥ አዘጋጅተው ለልጆቻቸው የሚጠቀሙበት ሁኔታም መኖሩንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ባህላዊ ሕክምና የሚሰጡባቸው ከ1 ሺህ በላይ ዕጽዋቶች መገኛ አገር መሆኗን የተናገሩት ሎሬት ዓለሙ፣ በማህበሩ ሥር የታቀፉ 981 የባህል ህክምና አዋቂዎች እንዳሉም ገልጸዋል።
እንደእርሳቸው ገለጻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት የባህል ህክምናን ለመደገፍ የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ነው፡፡
ለአብነትም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አንድ ዳይሬክቶሬት አቋቁሞ በባህል መድኃኒቶች ላይ የተለያዩ ጥናትና ምርም ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለማህበሩ የምርምር ማዕከል ለማቋቋም እያደረገ ያለው ጥረት የሚጠቀስ መሆኑን ነው ሎሬት ዓለሙ ያስታወቁት፡፡
የባህል መደኃኒቶች በዘመናዊ መንገድ ተዘጋጅተው ለህብረተሰቡ የሚቀርቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፍላጎት እጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ከአካባቢው የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር ያደረገውን ትስስር ወደ ማህበሩ በማምጣት በተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የማህበሩ አባላት በተለይ በአሁኑ ወቅት ዓለምን ያስጨነቀው የኮቪድ-19 ወረርሽንን ለመከላከል የራሳቸውን የምርምርና የጥናት ሥራዎች እየሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስትቲዩት የባህልና ዘመናዊ መድኃኒቶች ዳይሬክቶሬት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ተካ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በባህል መድኃኒትም ሆነ በባህል አዋቂዎች ደረጃ በርካታ ግብዓት ያላት ቢሆንም በተፈለገው መንገድ ሳትጠቀም መቆቷን ተናግረዋል፡፡
ኢኒስቲትዩቱ ከእጽዋት፣ ከእንስሳትና ከማዕድናት የሚገኙና ለመድኃኒት የሚውሉ ግብአቶች ላይ ሳይንሳዊ ምርምሮችን እንደሚያደርግም አስረድተዋል።
በአሁኑወቅት ለባህል ህክምናው እየተሰጠ ያለው ትኩረት የተሻለ ቢሆንም ገና ብዙ እንደሚቀረው ወይዘሮ ፍሬህይወት ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክቶሬቱ በመላ አገሪቱ ለሚገኙ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ከሚሰጠው ድጋፍ መካከል የተለያዩ ስልጠናዎች እንደሚጠቀሱ ገልጸው፣ በምርምር ሥራ እንዲሳተፉ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡