ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ዜጎች ቁጥር እንዲያሻቅብ ማድረጉን ፋኦ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ዜጎች ቁጥር እንዲያሻቅብ ማድረጉን ፋኦ ገለጸ
አዲስ አበባ 13/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ችግርን እንዲባባስ ብሎም ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ቁጥርም እንዲያሻቅብ ማድረጉን የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) አስታወቀ።
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፋጡማ ጃማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የበርሃ አንበጣ ወረራ በግብርናው ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ እጥፍ ድርብ እድርጎታል።
በቅድመ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊዎች እንደነበሩ አስታውሰው፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ደግሞ አሁን ላይ የተረጂዎች ቁጥር ከዚህ በላይ እንዲንር ማድረጉን ገልጸዋል።
አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን በበርሃ ወረራ ሳቢያ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና በመሻሻል ላይ ቢሆንም ዓለም ዓቀፋዊው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ግን ስኬቶችን ለማስቀጠል በእጅጉ አሉታዊ ተጽዕኖውን እንዳጎላው ነው የተናገሩት።
ድርጅታቸው ኮቪድ-19ን ወረርሽኝና ሌሎች አደጋዎችን የሚያስከትሉትን የምግብ ዋስትና ችግር ለመቋቋም ለኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ገልጸው፤ በጉዳዩ ላይ በቀጣይ ወር ሪፖርቱ እንደሚወጣ ገልጸዋል።
በኮቪድ-19 ሳቢያ ለ70 በመቶው ህዝብ የኑሮ መሰረት የሆነው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ መጎዳቱን ገልጸው፤ በተለይም የቡና፣ የቅባት እህሎች፣ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የስጋ ወጪ ንግድ መጎዳቱን ነው ተወካይዋ የገለጹት።
ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በተለይም ከአንበጣ ወረራ ቁጥጥር ሂደትና ከኑሮ ማሻሻያዎች ድጋፍ ጋር በተያያዘ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸው፤ በዚህም በተወሰነ መልኩ በዜጎች ገቢ ደረጃ መቀዛቀዝ እንዳለ ጠቁመዋል።
የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮቪድ-19 ከተከሰተ በኋላ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያሉ፣ አረጋውያን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችና በዕለት ገቢ የሚተዳደሩ 15 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በግንቦት ወር መጨረሻ ለኢዜአ መግለጹ ይታወሳል።