ኩባ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ትሰራለች --- በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
ኩባ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ትሰራለች --- በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር
አዲስ አበባ፣ሐምሌ 13/2012 (ኢዜአ) ኩባ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስ ተናገሩ፡፡
ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በትምህርት፣ በስፖርት፣ በሳይንስ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ማስፋት እንደምትሻም አምባሳደሯ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ቪልማ ቶማስ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መልካም ቢሆንም በተለያዩ ዘርፎች ሊጠናከር ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ እና ኩባ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብራቸውን እያሳደጉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል ፡፡
ሁለቱ አገራት እ.አ.አ ከ1978 ጀምሮ በጤናው ዘርፍ ትብብር ፈጥረው እየሰሩ መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደር ቶማስ፣ የኩባ የህክምና ዶክተሮች ኢትዮጵያን በትምህርት እና በስልጠና ዘርፎች በመደገፍ ሙያዊ እገዛ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አመልክተዋል።
"ኩባዊያን ዶክተሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሰጡት ጠቀሜታ አንጻር ያላቸው ቁጥር ብዙ ነው የሚባልበት ደረጃ ላይ ባይሆንም በዚህ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋራ ያለንን ትብብር በቀጣይ ማስፋት እንችላለን" ብለዋል።
ሁለቱ አገራት በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንም ነው አምባሳደር ቪልማ ያስረዱት፡፡
እንደ አምባሳደር ቶማስ ገለጻ ሁለቱ አገሮች በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ መደጋገፍ ለመፍጠር በዓለም አቀፍ መድረኮችም ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል፡፡
አሜሪካ በኩባ ላይ የጣለችውን የኢኮኖሚ፣ የገንዘብ እና የንግድ ማዕቀብ ያወሱት አምባሳደሯ፣ ማዕቀቡ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ በመንግስታቱ ድርጅት እና በአፍሪካ ህብረት መወገዙን ገልጸዋል።
"በእዚህ ላይ ኢትዮጵያ ለያዘችው ትልቅ አቋም ምስጋና ይገባታል” ብለዋል
"ኩባ በዓለም ላይ የሰለጠነ የሰው ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንዲመጣ በዘርፉ ያላትን ተሞክሮ ማካፈል ትሻለች" ሲሉም አምባሳደሯ ገልጸዋል፡፡
አገራቸው በዚህ ረገድ ያላት ስኬታማ በዩኔስኮ እውቅና ያገኘና በብዙ የዓለም አገራትም በተሳካ ሁኔታ ጥቅም ላይ መዋሉን አምባሳደር ቶማስ ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ በትምህርቱ ዘርፍ ከኩባ ልትጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና የኩባ ግንኙነት 45 ዓመታትን ማስቆጠሩን አስታውሰው "ይህም ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ያደርጋቸዋል" ብለዋል፡፡