ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ስራዎች ላይ የበጀት እጥረት ዋና ተግዳሮት መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ስራዎች ላይ የበጀት እጥረት ዋና ተግዳሮት መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ ሀምሌ3/2010 ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል ስራዎች ላይ የበጀት እጥረት መኖሩን የፌዴራል ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር ማሻገር ወንጀል ተከላካይ ግብረ ኃይል ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አስተባባሪ ወይዘሮ ፈቲያ ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት የግብረ ኃይሉ አባል ተቋማት የበጀት እጥረት ችግር ላለፉት ሁለት ዓመታት የዘለቀና በስፋትም የሚታይ ችግር ነው። ግብረ ኃይሉ 35 የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ አባል ተቋማትንና አደረጃጀቶችን ያካተተ ሲሆን አብዛኞቹ ተቋማት ህገ ወጥ ዝውውር የመከላከሉን ስራ በዋና ስራዎቻቸው እቅድ ውስጥ ያለማካተትና በጀት ያለመመደብ ችግሮች ይስተዋልባቸዋል ብለዋል። በመሆኑም ተቋማቱ የህገ ወጥ ስደት የመከላከል ስራዎችን በታቀደውና በሚፈለገው መጠን ለማከናወን እንዳልቻሉ ነው የተናገሩት። ግብረ ኃይሉ አባል ተቋማቱ ለስራቸው አስፈላጊውን ፈንድ በበጀታቸው ላይ አካተው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግም ከህገ ወጥ ዝውውር መከላከል ብሄራዊ ምክር ቤት ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ይህን የመከላከል ስራዎችን በዕቅዶቻቸው ላይ ማካተት የሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸው እነዚህ ስራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። ወይዘሮ ፈቲያ እንደተናገሩት አባል ተቋማቱን የሚወክሉ ኃላፊዎች መቀያየርና በባለሙያዎች መተካትም ስራዎችን በሚፈለገው መጠን ማስቀጠል ባለማስቻሉ ተቋማት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ኃላፊዎችን እንዲቀይሩ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ነው። በሌላ በኩል ክልሎች ላይ የሰዎችን ህገ ወጥ ዝውውር መከላከል ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር አንዳንዶቹ ዘንድ የበጀት ብክነት ሌሎቹ ዘንድ ደግሞ እጥረት መኖሩን አንስተዋል። ይህንን ችግር መፍታት የሚያስችል የፕሮጀክቶች በጀት የማቀናጀት ስራ ለማከናወን የሚያስችል ጥናት መጠናቀቁንና ከ2011 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩል ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ከአገሪቷ የሚወጡባቸው የመውጫ ድንበሮች አካባቢ የሚገኙ ክልሎች ላይ የህገ ወጥ ተዘዋዋሪዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆን እየፈጠረ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችንም አንስተዋል ወይዘሮ ፈቲያ። እነዚህ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የተያዙ ዜጎችን ወደ መጡባቸው ክልሎች የመመለስ ስራዎች ላይም ዜጎች ለእንግልት እንደሚዳረጉም ጠቅሰዋል። በመሆኑም ክልሎች ይህንን ስራ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ለመስራት እንዲችሉና ዜጎችን ከእንግልት ለመታደግ የክልሎች መግባቢያ ሰነድ ተዘጋጅቷል ብለዋል። በሰነዱ ላይ በክልሎቹ ውይይት የተደረገ ሲሆን በቀጣይም ተፈራርመው ወደ ስራ እንደሚገቡ ነው የገለጹት። እንደ ወይዘሮ ፈቲያ ገለጻ በክልሎች የህገ ወጥ ስደት አስከፊነት ላይ ግንዛቤ የሚሰጡ ስራዎች ረገድ አሁንም ክፍተቶች ቢኖሩም በኪነጥበብ ስራዎች የተደገፉ ስራዎች በመሰራታቸው ለውጥ ተገኝቷል። የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን የህገ ወጥ ስደት አስከፊነት ለማሳየት በሚችልና ወጥነት ባለው መልኩ ለመስራት የሚያስችል መመሪያ የተዘጋጀ መሆኑንም አክለዋል። ለስደት ተመላሾች የሚሰጡ ድጋፎች በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ ያለመሆንና ድጋፉን ማግኘት የሚገባቸውን ሰዎች ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል። በመሆኑም ለስደት ተመላሾች የሚሰጡ ድጋፎችን ለማሻሻል፣ ወጥ ለማድረግ የሚያስችልና ድጋፍ ማግኘት የሚገባቸው የስደት ተመላሾች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ ለማስቻል የተጎጂዎች ድጋፍ አሰጣጥ ረቂቅ መመሪያም ተዘጋጅቷል ብለዋል። በ2009 ዓ.ም ብቻ ከአገሪቷ የተለያዩ የመውጫ በሮች ላይ 8 ሺህ 524 ዜጎች በህገ ወጥ መንገድ ለመውጣት ሲሞክሩ መያዛቸውን ከፌዴራል ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር ማሻገር ወንጀል ተከላካይ ግብረ ኃይል ሴክሬተሪያት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።