በሐረሪ ኮሮናን በመከላከል መዘናጋት ይስተዋላል - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ኮሮናን በመከላከል መዘናጋት ይስተዋላል
ሐረር፣ ሐምሌ 13 / 2012 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው ቸልተኝነት ትኩረት እንዲሰጠው ተጠቆመ።
ህብረተሰቡን ከበሽታው ለመታደግ የቅስቀሳ ስራዎችን ለማጠናከር አቅጣጫ መቀመጡን የክልሉ ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይሉ ገልጿል፡፡
እራሳቸውን ከቫይረሱ ለመጠበቅ እየተጠነቀቁ ቢሆንም በአንዳንድ የህብረተሰቡ ክፍል የሚስተዋለው ቸልተኝነት ስጋት እንደፈጠረባቸው በሐረር አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ተስፋዬ ጥላሁን ለመጠንቀቅ ጥረት ቢያደርጉም በአገልግሎት መስጪያ አካባቢዎች ህብረተሰቡ በሽታውን የመከላከያ ዘዴዎች ያለመጠቀም ሁኔታ እንዳለ መታዘባቸውን አመልክተዋል።
በተለይም በገበያ፣ ሆቴልና ትራንስፖርት አጠቃቀም ላይ መጠጋጋትና መጨናነቅ ይስተዋላል ሲሉ ጠቅሰዋል።
ይህም የተለመደው ማህበራዊ ህይወት መመለሱን እንደሚያሳይና በሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጠውም ጠቁመዋል።
ቫይረሱን ለመከላከል የሚተላለፉ መልዕክቶችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የሚስተዋለው መዘናጋት እንዳሰጋቸው የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አለምነሽ ተሰማ ናቸው።
በእሳቸው በኩል ዘወትር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በመጠቀም ጭምር አስፈላጊውን ጥንቃቄ ለማድረግ ቢጥሩም የሌላው መዘናጋት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
መንግስትም በአካባቢው እያከናወነ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጥና ቁጥጥር ሰራ ማጎልበት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በሐረር ሸዋበር በሚገኘው የገበያ ስፍራ ሲገበያዩ የነበሩት አቶ አብዲ ኡስማን በሰጡት አስተያየት ርቀታቸውን ጠብቀው በመገበያየት የበኩላቸውን ጥንቃቄ ቢያደርጉም በብዙዎች ዘንድ ግን የሚስተዋለው ቸልተኝነት አስጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በአካባቢው ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች መኖራቸው እየታወቀ ርቀትን ያለመጠበቅና ጭንብል ያለመጠቀም ሁኔታ እየተለመደ በመምጣቱ በሽታውን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ለማስተግባር ትኩረት እንዲሰጠው ጠቁመዋል።
በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ያለው ማህብረሰብ ለጊዜውም ቢሆን ከተለመደው የተቀራረበ ግንኙነት በመቆጠብ የጥንቃቄ መልዕክቶችን መተግበር ይገባዋል ብለዋል።
መንግስትም ህዝቡን ከበሽታው ለመታደግ በላቀ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለበትም አመልክተዋል።
በክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል የግንዛቤና ቅስቃሳ ኮሜቴ ጸሐፊ አቶ ሬድዋል መሀመድ በበኩላቸው ቫይረሱን በመከላከሉ ረገድ ህብረተሰቡ ርቀት ያለመጠበቅና ጭንብል ያለመጠቀም ክፍቶች እንዳሉ ብለዋል።
ለዚህም ቀደም ሲል በሁሉም ሴክተር ይከናወን የነበረው የቅስቀሳና ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መቀዛቀዝና በቅርቡ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ ይህንን ችግር በመገንዘብ ህብረተሰቡን ከበሽታው ለመታደግ በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የቅስቀሳና ህግን የማስከበር ስራዎችን ለማጠናከር አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡