በሲዳማ ክልል የህዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ የሚመልስ አደረጃጀት እየተዘረጋ ነው...ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የህዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ የሚመልስ አደረጃጀት እየተዘረጋ ነው...ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ
ሀዋሳ ሐምሌ 12/2012( ኢዜአ) በሲዳማ ክልል የህዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል አደረጃጀት እየተዘረጋ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አደረጃጀቱ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የአዳዲስ ዞኖች መዋቅርና ነባር ወረዳዎችን መልሶ የሚያጠናከር ስራ ነው።
ከዚህ በተጓዳኘም ክልሉ የሚመራበት ስትራቴጂና ዓመታዊ እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይ የክልሉ አደረጃጀት በዋናነት የህብረተሰቡን ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበና ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን ለማከናወን በሚያስችል መልኩ የሚዘረጋ መሆኑን አስታውቀዋል።
"አዲስ መዋቅር ለመዘርጋት ጥናት ተካሂዷል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ረገድ ዋና አካሄድ የሚገኘውን ሀብት በቁጠባ በመጠቀም ውጤት ለማስመዝገብና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት ማመቻቸት መሆኑን ገልጸዋል።
ያካሄዱት ጥናት ይህንን የሚደግፍ መሆኑን አመልክተው በዚህም የሲዳማ ክልል በዋናነት በአራት ዞኖች ይደራጃል ብለዋል።
የሚደራጁት ዞኖች ባህሪ ምክር ቤትና ብዛት ያላቸው መስሪያ ቤቶች የሚኖራቸው ሳይሆን 30 ወረዳዎችን በመፍጠርና የመረጃ ፍሰቱን በማቀላጠፍ በቅርበት ድጋፍ እንዲሰጡ የሚደረግ መሆኑን አመልክተዋል።
በስድስት ካቢኔ ደረጃ የሚዋቀርና አስተባባሪ ያለው አንድ ዞን ከ50 የማይበልጥ የሰው ኃይል ያለው ሆኖ ዋና ተልዕኮው ክልልና ወረዳን ድልድይ ሆኖ ማገናኘት እንደሚሆን አስታውቀዋል።
ለጊዜው ተጨማሪ ወረዳን ለመክፈት ጥናቱ እንደማያሳይ ጠቁመው ወረዳን እያሰፉ መሄድ ወጪን ማብዛት እንጂ ህዝቡ የሚፈልጋቸውን መሠረታዊ የሆኑ የመንገድ ፣ውሃ፣ጤና፣ ትምህርትና ሌሎችንም አቅርቦት ለሟሟላት አያስችልም ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ "ክልል መሆን በራሱ ትልቅ ሃብት የሚያስገኝና የፈለጉትን ማድረግ የሚያስችል አድርጎ የሚያዩ ወገኖች አሉ፤ እኛ ግን ይህ እንዳልሆነ በፊትም እናውቃለን፣አሁንም በተጨባጭ እያየን ያለነው ይሄንኑ ነው " ብለዋል።
ባለው ውስን ሀብት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ድህነትን መዋጋት፣መልካም አስተዳደርን ማስፈንና የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ቅድሚያ በመስጠት ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ደስታ ገለፃ በሚቀጥሉት ዓመታት የትኩረት ማዕከል ሆኖ የሚቀጥለው ወጣቶችን የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድርግ ነው።
በተመረጡ ዘርፎች ከ100 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማደራጀት በልማት ፕሮጀክቶች ግንባታና በሌሎችም ገበያ ተኮር በሆኑ የስራ መስኮች ለማሰማራት ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።