ቀጥታ፡

የዳያስፖራ ማኅበር በሁከቱ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ከመንግስት ጋር ይሰራል

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 12/2012  (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ማኅበር ከሰሞኑ ተፈጥሮ በነበረው ሁከት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ ከመንግስት ጋር እንደሚሰራ ገለጸ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከማኅበሩ አባላት ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት አድርጓል።  

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ስዩም እና የማኅበሩ የቦርድ አባል አቶ እድሪስ መሃመድ የሆነው ነገር ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ገጽታ የሚያሳይ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።

አልፎ አልፎ በሚፈጠር ችግር የሚደርሰው ጥፋት በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንደሚያሳድርም ተናግረዋል።

በተለይም በብዙ ድካም የሚመጣውን የውጭ ኢንቨስትመንት መጉዳት ረጅም ጊዜ የሚቆይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስገንዝበዋል።

መሰል ጥፋት እንዳይፈጠር ለመከላከል የኅብረተሰቡን የመደማመጥ ባሕል ማዳበር ይገባል ነው ያሉት።

መገንባት እንደ ማፍረስ ቀላል አለመሆኑን የተናገሩት የማኅበሩ አመራር አባላት፤ የጥፋት ድርጊት በዚሁ እንዲያበቃ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

አገር የከፋ ፈተና ላይ እንዳትወድቅ ሌሎች ካጋጠማቸው ኪሳራ ትምህርት መውሰድ ተገቢ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የደረሰው ጥፋት አሳዛኝ መሆኑን በመግለጽ ማኅበሩ ከዚህ ጥፋት ለማገገም የሚደረገውን ጥረት  እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም መንግስት ከሚያደራጀው ግብረ ኃይል ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም