ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የባሕሪይ ለውጥ በሚያመጡ ተግባራት ላይ ማተኮር አለባቸው -- ጥናት

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 12/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ የባሕሪይ ለውጥ በሚያመጡ ተግባራት ላይ አተኩረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አንድ ጥናት አመለከተ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በአመራር አባላቱና ባለሙያዎቹ ሁለቱን ከተማ አስተዳደሮችና የሰባት ክልሎች ዋና ከተሞችን በማካተት ያካሄደውን ጥናት ይፋ አድርጓል።

ጥናቱ በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚገኙ 966 ሰዎችን መጠይቅ በማስሞላት የተሰራ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 100 ሰዎች ቃለ መጠይቅ የተደረላቸው ናቸው።

ባለሥልጣኑ መገናኛ ብዙኃን በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ያበረከቱትን አስተዋፅኦና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራቸውን የቃኘበት አገራዊ ጥናት እንዳሳየው ኅብረተሰቡ የባሕሪይ ለውጥ አምጥቶ በሽታውን መቆጣጠር እንዲቻል ሙያዊ ተግባራቸውን በጥራትና በጥልቀት መከወን ይጠበቅባቸዋል።

ለዚህም ወረርሽኙ በኅብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለውን ችግር መተንተን፣ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎችን ማቅረብና በክልሎች ያለውን የወረርሽኙን ይዞታ መዘገብ ይገባቸዋል ብሏል።

በተለይ ለወረርሽኙ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩና በሽታውን የተቆጣጠሩ አገራትን ልምድ ማጋራት እንደሚያስፈልግም ጥናቱ ጠቁሟል።

የቋንቋ ተደራሽነትን በማሳደግ ስለ ወረርሽኙ ያለውን ግንዛቤ ማስፋት እንደሚቻል ያመለከተው ጥናት፤ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን በማስተማሪያነት መጠቀም ያሻል ብሏል።

መንግሥትም በተለይ የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራውን እንዲያጠናክሩ ድጋፍ እንዲያደርግ በጥናቱ ተጠይቋል።

መገናኛ ብዙኃን የትራንስፖርት፣ የባንክ፣ የውሃና የኤሌክትሪክ ክፍያ ቦታዎች፣ የገበያና የመናኽሪያ አካባቢዎችን ከወረርሽኙ ስርጭት አኳያ በዘገባቸው እንዲቃኟቸውም አሳስቧል።

የሃይማኖት አባቶችና የጤና ባለሙያዎችን መልዕክቶች በማሰራጨት በቅንጅትና በመናበብ ቢሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም አመላክቷል።

ወረርሽኙን ለመከላከል የሚካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በበጎ ፈቃደኝነት ብቻ ሳይሆን፤ በበጀትም ተደግፎ በገጠርም እንዲስፋፋ ማድረግ አስፈላጊ ስለመሆኑም ጥናቱ ጠቁሟል።

በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላትም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራን ቤት ለቤትና በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች በመስጠት የባሕሪይ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ማጠናከር አለባቸው።

በገጠራማ አካባቢዎች የአስተዳደርና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ቤት ለቤት ቅስቀሳ ማድረግ፣ በቢልቦርድና በፖስተሮች ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ማስተማር ያስፈልጋል ብሏል።

በወረርሽኙ ሳቢያ ሥራ የተቋረጠባቸውና አቅም የሌላቸው ሰዎች የዕለት ጉርስ ፍለጋ ከቤት ለመውጣት ስለሚገደዱ መንግሥት የሃብት ማሰባሰብና የመደገፍ ሥራ ቢያከናውን የወረርሽኙን ስርጭት በመቀነስ ውጤት እንደሚያስገኝ ተገልጿል በጥናቱ።

ጥናቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎችና ፆታዎች ያካተተ ሲሆን፤ ዕድሜያቸውም ከ21 በላይ ነው።

የጥናቱ ተሳታፊዎች የትምህርት ደረጃ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው 37 ከመቶ፣ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ዲፕሎማ ያላቸው 18 ነጥብ 4 በመቶ ሲሆኑ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ደግሞ 6 ነጥብ 8 በመቶውን ሸፍነዋል።

ከእነዚህም የመንግሥት ሠራተኞች 44 ነጥብ 3፣ በንግድ ሥራ የተሰማሩ 20 ነጥብ 5 ፣ በግል ሥራ የተሰማሩ ደግሞ 12 ነጥብ 5 በመቶ ናቸው።

ወረርሽኙን አስመልክቶ መረጃ በማድረስ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ግንባር ቀደም ሲሆኑ፣ በተሽከርካሪዎችና በጤና ተቋማት የሚካሄዱ ቅስቀሳዎችና የጤና ሚኒስትሯ የዶክተር ሊያ ታደሰ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተከታዮቹን ደረጃዎች መያዛቸውን ጥናቱ አሳይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም