ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም - ኢዜአ አማርኛ
ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 12/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ችግርችን ለመፍታት ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ውጪ ሌላ አማራጭ አለመኖሩን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ማህበር አመለከተ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ማህበር አመራር አባላት ጋር የፓናል ውይይት አካሂዷል።
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ትኩረት ያደረገው ውይይት በተለይ ከአርቲስት ሐጫሉ ግድያ በኋላ በተፈጠረው ሁኔታ ዙሪያ ያጠነጠነ ነው።
አርቲስቱ ሕይወቱ ካለፈ በኋላ በተፈጠረው ግርግር ሕይወት ማለፉና ንብረት መውደሙ ያልተገባ ድርጊት እንደነበር ያነሱት ተወያዮቹ፤ ይህም ኢትዮጵያዊ እሴት ያለመሆኑን አስምረውበታል።
ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ተወያይቶ መፍታት ወሳኝ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ሥዩም በሰጡት አስተያየት ''ከማውደም የምናተርፈው ነገር የለም፤ ልንማር ይገባል'' ብለዋል።
''ኃይልን እንደመፍትሄ መጠቀም ሊበቃ ይገባል'' ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤''መደማመጥን መለማመድ አለብን'' ይላሉ።
ወጣቱም ሐሳቦችና ጥያቄዎች ካሉት የሚደመጥበት ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ከተደማመጥን መፍትሄ የሌለው ጥያቄ አይኖርም ሲሉም አክለዋል።
''በኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ ስልጣንን መያዝ የሚቻለው በዴሞክራሲና በምርጫ ብቻ ነው'' ያሉት ደግሞ ሌላው ተወያይ አቶ ኢድሪስ መሐመድ ናቸው።
ልጆችን ከመሠረቱ አንጾ በማሳደግ ወላጆች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።