ቀጥታ፡

የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አንድ አቋም ሊኖረው ይገባል

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 12/2012 (ኢዜአ)  የሕዳሴውን ግድብ አስመልክቶ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አንድ አቋም ሊኖረው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ማኅበር አመለከተ።

ማኅበሩ የአሜሪካ መንግሥት በግድቡ ላይ ገለልተኛ አቋም እንዲኖረው ሲሰራ መቆየቱንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከማኅበሩ አባላት ጋር በወቅታዊና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የፓናል ውይይት አካሂዷል።  

ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅም የሚገነቡት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ደርሷል።

የዳያስፖራ ማኅበር አባላቱ ግድቡ በውጭው ማኅበረሰብ ዘንድም እንደ ዓይን ብሌን የሚታይ መሆኑን በመጥቀስ ወቅቱ ያለ ልዩነት ድጋፍ የምናደርገበት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ስዩም ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ እስከ ጫፍ የተንቀሳቀሱበት ጉዳይ ቢኖር የሕዳሴው ግድብ ነው ይላሉ።  

ግድቡ የሕይወትና የሉዓላዊነት ጉዳይ በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በዚህ ሊደራደር እንደማይገባም አመልክተዋል።  

"ፖለቲካና ልማትን መለየት ያስፈልጋል" ያሉት አቶ አብርሃም ልዩነት ያለና የሚጠበቅ ቢሆንም ዓባይ ላይ ሁላችንም አንድ አቋም ሊኖረን ያሻል ባይ ናቸው።     

እንደ አቶ አብርሃም ገለጻ ግድቡ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ስለደረሰ የውጭው ማኅበረሰብ ከጫፍ ጫፍ ሊንቀሳቀስ ይገባል።   

በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እየተደረገ ስላለው ንቅናቄም አብራርተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ "ዳግማዊ አድዋ ነው" ያሉት ደግሞ የማኅበሩ የቦርድ አባል አቶ እድሪስ መሀመድ ናቸው።

ሌላው የማኅበሩ የቦርድ አባል ሻምበል ብርሃኑ ተስፋዬም በውጭ ያለው ማኀብረሰብ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ በቅርበት መስራት ያስፈልጋል የሚል ሀሳብ አንስተዋል።

"በውጭ ላለው ማኅበረሰብ ስለ ግድቡ ተገቢውን ቅስቀሳ በማድረግ ማሳተፍ ይገባል" ያሉት ሻምበል ተስፋዬ ዳያስፖራው እንደ ሌላ አካል መታየት የለበትም ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም