መንግስት በአጥፊዎች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በአጥፊዎች ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ
ሀምሌ12/2012 (ኢዜአ) መንግስት በቅርቡ በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ግርግር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸው አለበት ተብለው በተጠረጠሩ አካላት ላይ እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር ተግባር እንደሚደግፉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ሰኔ 22/2012 አመሻሽ ላይ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ በተቀነባበረ ሴራ በጥይት ተመቶ ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የንጹሃን ሰዎች ህይወት አልፉል፣ዜጎች ከመኖሪ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፣የመኖረያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች በእሳት ወድመዋል እንዲሁም ንብረቶች ተዘርፈዋል።
በዚህ እኩይ ተግባር ተሳትፎ በነበራቸው አካላት ላይ መንግስት የጀመረውን የህግ የበላይነትን የማረጋገጥን ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በህዝቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ባደረጉ እንዲሁም በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ባደረሱ አካላት ላይ መንግስት እየወሰደ ያለው ርምጃ ተገቢ መሆኑን የገለፁት አቶ ምህረት ጌታሁን ናቸው።
እንደ አቶ ምህረት ጌታሁን ገለፃ የህግ የበላይነት ካልተከበረ ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲበራከቱ ስለሚያደርግ ጥፋተኞችን አድኖ ለፍርድ ማቅረብ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም።
ህዝቡም ከመንግስት ጎን በመቆም ጥፋተኞችን ወደ ህግ ለማቅረብ በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል አቶ ምህረት።
ሀገር መውደድ ማለት ወንጀሎች ሲፈፀሙ ሰምቶ እንዳልሰሙና አይቶ እንዳላዩ ዝም ማለት ሳይሆን ጥፋተኞችን በማጋለጥ ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግን ያካትታል ያሉት አቶ ምህርት እሳቸውም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።
አቶ ወርቅነህ አበበ በበኩላቸው ̎ህዝብ የመንግስት አይንና ጀሮ በመሆኑ መንግስት በሚወስዳቸው ህግ የማስከበር እርምጃዎች የህብረተሰብ ሚና በእጅጉ ያስፈልጋል̎ ብለዋል።
ያለ ህዝብ ተሳትፎ የአንድን ሀገር ሰላም ሙሉ ለሙሉ ማስጠበቅ አዳጋች ስለሚሆን ህዝቡ ትብብር ማድረግ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል አቶ ወርቅነህ።
መንግስት የሰባዊ መብት ጥሰት ባደረሱ አካላት ላይ የጀመረውን ህግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለፁት ደግሞ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አወል ሱልጣን ናቸው።
እንደ አቶ አወል ገለፃ የመንግስት ዋና ሚና የህግ የበላይነትን በማስከበር የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅና ማህበረሰቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም እንዲገባ ማድረግ ነው።
መንግስት ለብዙ ጊዜያት የፓለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በሚል በርካታ ስተቶች ሲፈፀሙ በሆደ ሰፊነት ያሳለፈ ቢሆንም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በጥፋት ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት በሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርሱ ቆይተዋል ብለዋል።
̎ተጠያቂነትን ለማስፈን የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት̎ ብለዋል።
በመጨረሻ አቶ አወል መንግስት ህግን ለማስከበር በሚወስደው ርምጃ የሰባዊ መብት ጥሰት እዳይፈፀም ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት መክረዋል።