ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ እናጠናቅቀዋለን ... የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች

ባሀርዳር (ኢዜአ) ሐምሌ 11 ቀን 2012 ዓም ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ኤዜኣ ያነጋገራቸው የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ ።በአማራ ክልል በዚህ ዓመት በህብረተሰቡ ተሳትፎ 2ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራና የቦንድ ግዥ መከናወኑንም የክልሉ የህዳሴ ግድብ የህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ገልጿል ።

የከተማዋ ነዋሪና የውኃ ሃይድሮሎጂስት ባለሙያ አቶ አፈወርቅ ተክለማርያም ለኢዜአ እንደገለፁት ሃገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ የምታደርገውን ሽግግር የሚሳካው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለውጤት ሲበቃ ነው ።

የኢትዮጵያ ህዝብ በገንዘቡ ፣ በእውቀቱና በጉልበቱ አስተዋፅኦ በማድረግ ውጤቱን በጉጉት የሚጠባበቀውና የትውልድ አሻራ የሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ በማንኛውንም ምክንያት ሊደናቀፍ እንደማይችል ተናግረዋል።

ግድቡን ለውጤት እንዳይበቃ ቀን ከሌሊት እየሰሩ ካሉት ኃይሎች ጋር ተባባሪ የሆኑ ቡድኖችና ግለሰቦች ሀገር ሻጮች ናቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል ።

“ሃገርን መክዳት የኢትዮጵያዊያን አባቶቻችን ታሪክ አልነበረም” ያሉት አቶ አፈወርቅ “እነዚህን ኃይሎች በአንድነት ሆነን በመታገል የግድቡን መጠናቀቅ ማብሰር አለብን” ብለዋል ።

የውኃ ሙሌት ስራውን ለመጀመር እየተደረገ ያለው ጥረትም በእቅዱ መሰረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በህዳሴው ግድብ ላይ ጠንካራ አቋም ይዘው በአንድነት ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለግድቡ ግንባታ ከ16 ሺህ ብር በላይ የቦንድ ግዥ በመፈፀም የበኩላቸውን ድጋፍ ማበርከታቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸው አስረድተዋል ።

“ለታላቁ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ ህዝብ በሃሳብም ሆነ በተግባር አንድ ሆኖ መቆም ያለበት ወሳኝ ወቅት ነው” ያሉት ደግሞ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዋናቸው ታሪኩ ናቸው ።

“በግድቡ ስራ እየተሰሩ ያሉት ተግባራት ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን ምሁራን በእውቀታቸው፣ ህዝቡ በገንዘቡና በጉልበቱ እንዲሁም ፖለቲከኞች ለዓለም እውነታውን በማሳወቅ ተባብረን ልንሰራ ይገባል” ብለዋል ።

“ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን በዓለም አደባባይ በኢኮኖሚና ባላቸው ተሰሚነት ከፍታ የሚታይበት መውጫ መንገድ ነው” ሲሉም አብራርተዋል ።

የኢትዮጵያ ህዝብም ለግድቡ ድጋፍ ከማድረግ በዘለለ ከውስጥም ከውጭም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተጽዕኖዎችን በማሸነፍ ሁሉም በአንድነት በመቆም ታሪክ ሰሪ መሆን እንደሚገባው ጠቁመዋል ።

“ግድቡ ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ያስተሳሰረ ነው” ያሉት አቶ ዋናቸው ለፍፃሜ እስኪደርስ ድረስ እስከ አሁን ያበረክትቱን አስተዋፅኦ አጠናክረው አንደሚቀጥሉ ገልፀዋል ።

“ግድቡ የውኃ ሙሌት የሚከናወንበት ወቅት በመሆኑ ሁሉም ከመንግስት ጎን በመቆም በገንዘብ ፣ በእውቀትና በጉልበት በመደገፍ የዜግነት ድርሻውን ማበርከት አለበት” ብለዋል ።

የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ላቀ ጥላየ በበኩላቸው በክልሉ በ2012 ዓም በጀት ዓመት በህብረተሰቡ ተሳትፎ 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራና የቦንድ ግዥ መከናወኑን ገልፀዋል ።

“በአባይ ጉዳይ ቀስቃሽና ተቀስቃሽ ባለመኖሩ ግድቡን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃይሎች ህብረተሰቡ በአንድነት ቆሞ ሊታገላቸው ይገባል” ብለዋል ።

የክልሉ ወጣት አደረጃጀቶችም እስከ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ 510 ሚሊዮን ብር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቦንድ ግዥ ለመሰብሰብ አቅደው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል ።

ግድቡ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከክልሉ ህዝብ በቦንድ ግዥ 1ቢሊዮን 187 ሚሊዮን ብር ፤ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ደግሞ 26 ቢሊዮን ብር የሚገመት አስተዋፅኦ ማድረጉን ከማስተባበሪያ ፅህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም