ቀጥታ፡

አየር መንገዱ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካጋጠመው ጫና በአንድ አመት ጊዜ እንደሚያገግም አስታወቀ

አዲስ አበባ ሀምሌ 11/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮናቫይረስ  ወረርሽኝ  ካጋጠመው ጫና በአንድ አመት ጊዜ  አገግሞ ወደ ነበረበት ቁመና እንደሚመለስ አስታወቀ።

የኮቪድ-19 ወረረሽኝ መከሰት በርካታ አየር መንገዶች በረራቸውን በዘጉበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስቸጋሪውን ወቅት ወደ እድል በመቀየር በካርጎ አገልግሎት መቀጠሉ ይታወሳል።

አየር መንገዱ ስኬታማ ጉዞውን በመቀጠል በአቪየሽን ኡንዱስትሪ ከአፍሪካ አህጉር በቀዳሚነት ስፍራ ሲቀመጥ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አራተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጫ ተሰጥቶታል።

በወረርሽኙ የተነሳ ተቋርጦ የነበረው የመንገደኞች በረራ በአሁኑ ወቅት ተጀምሮ ለ38 የአውሮፓ አገሮች የበረራ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዓለም አቀፍ አገልግሎት ዋና ኃላፊ አቶ ለማ ያዴቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች ድርጅቱ ወደ ነበረበት ለመመለስ የአምስት አመት ጊዜ ይወስድበታል።

የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች አምስት አመት የማገገሚያ ጊዜ ቢያስቀምጡም አየር መንገዱ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ወደነበረበት ቁመና ለመመለስ አልሞ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ለማ ተናግረዋል።

''አየር መንገዱ የኢትዮጵያን ታላቅነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያበስር ድርጅት ነው'' ያሉት ኃላፊው፤ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማለት በትጋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

''የመንገደኞች አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተመልሶ ማገገም እስኪችል በካርጎ አገልግሎቱ ይቀጥላል'' ብለዋል።

አየር መንገዱ ከአፍሪካ ካሉት የካርጎ አገልግሎቶች ግዙፍ እና የተለያየ የአገልግሎት ክንፍ እንዳለው ጠቁመው፤ የአገልግሎቱን ድርሻ ከፍ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

አየር መንገዱ በቅርቡ 11 አዳዲስ አውሮፕላኖች እንደሚያስገባ ጠቁመው፤ ተጨማሪ የአየር ማረፊያ ስለሚያስፈልግ የአውሮፕላን ጣቢያ ያለው ከተማ ለመመስረት ዝግጅት እንዳለ ገልጸዋል።

ለዚህም የቦታ ርክክቡ ተጠናቆ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት 37 የጭነት እና 94 የመንገደኛ አውሮፕላኖች በድምሩ 131 አውሮፕኖች አሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም