በኦሮሚያ ክልል ሴቶች አደረጃጀቶች ከ120 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተተከለ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ሴቶች አደረጃጀቶች ከ120 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተተከለ
አዳማ ፣ሐምሌ 10/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር በሴቶች አደረጃጀቶች ከ120 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉ ተገለጸ።
የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የሴቶች አደረጃጀቶች በአርሲ ዞን ሎዴ የሎዴ ሄጦሳ ወረዳና ሁሩታ ከተማ ሄጦሳ በመገኘት ለአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ ዛሬ ከ2 ሺህ 500 በላይ ችግኝ ተከለዋል።
የክልል ሴቶች ፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙና አህመድ እንደገለጹት ለአርቲስቱ መታሰቢያ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር እንደቀጠለ ነው።
መረሃ ግብሩ እየተካሄደ ያለው በክልሉ ሁሉም ዞኖች ፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ የሴቶች አደረጃጀቶች መሆኑን ተናግረዋል።
ለአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ መታሰቢያ ብቻ ከ50 ሚሊዮን በላይ የችግኝ ተከላ መያዙን አስታውቀዋል።
በእነዚሁ አደረጃጀቶች እስካሁን ባለው ሂደት የእቅዳቸውን ከ70 በመቶ በላይ ማሳካታቸውን ገልጸዋል።
"አርቲስቱ የተሰዋለትን ዓላማ ከዳር ማድረስ የምንችለው የአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው ተፅእኖ ሴቶችና ህፃናት እንዳይጎዱ በአረንጓዴ አሻራ ላይ የድርሻችንን ስንወጣ ነው" ብለዋል።
የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ሊቀመንበር ወይዘሮ ሳዓዳ ዑስማን በበኩላቸው በክልሉ በሴቶች አደረጃጀቶች በኩል እስካሁን ከ120 ሚሊዮን በላይ የተለያየ ዝርያ ያለው ችግኝ መተከሉን አስታውቀዋል።
በሐምሌና ቀጣዩ ወር በወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች ብቻ በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር 1 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቶችና ሴቶች አንድ ላይ ተቀናጅተው በክልሉ ለመትከል ከታቀደው 3 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ ግማሹን ለመሸፈን በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።
ወይዘሮ ሳዓዳ የእስካሁኑ ሂደት በጥሩ አፈፃፀም እየተጓዘ መሆኑን ገልጸዋል።
አርቲስቱ የተሰዋለትን ዓላማ ለማሳካት በልማትና እድገት ላይ በሙሉ አቅማችን ለመስራት ለአረንጋዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ስራ ቅድሚያ መስጠት አለብን ያሉት ደግሞ የሁሩታ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀብታሙ ጋሪ ናቸው።
ከሶስት ሄክተር በላይ የተጎዳ መሬት በሴቶች አደረጃጀት ካርታ በማሰራት ማስረከባቸውን ጠቅሰው ችግኝ ከመትከል ባለፈ በቦታው በመመላለስ ችግኙን እንዲንከባከቡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በሎዴ ሄጦሳ ወረዳ እስካሁን ከ4 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬና የደን ችግኝ መተከሉም ተመልክቷል።