ቀጥታ፡

የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ለብሔራዊ ቤተመንግስት አድሳት የሚውል የ12 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2012 (ኢዜአ) የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ለብሄራዊ ቤተ መንግስት እድሳትና የሕዝብ መናፈሻ ግንባታ የሚውል የ12 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱ በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴና በፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ተጠሪ ቫሌሪ ቴኦ እንዲሁም በኢትዮጵያና በአፍሪካ ኅብረት የፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬድሪክ ቦንቴምስ መካከል ተፈርሟል።

በተደረገው ድጋፍ በመታገዝ የቤተ መንግስቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ እድሳትና የሕዝብ መናፈሻ ግንባታ ፕሮጀክት ይከናወንበታል ተብሏል።

ለፕሮጀክቱ የተደረገው ድጋፍ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እ.አ.አ መጋቢት 2019 ኢትዮጵያን በጎበኙ ጊዜ የአገሪቷን ቅርስ ለመጠበቅ እገዛ እንደሚያደረጉ የገቡትን ቃል ተከትሎ ነው።

ብሄራዊ ቤተ መንግስቱ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የተገነባ ሲሆን ከኢትዮጵያ ስመ ጥር የሕንጻ ግንባታዎች አንዱ መሆኑም ተጠቅሷል።

ቤተ መንግስቱ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ የማያውቅ ሲሆን አሁን የአገሪቷ ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤትና ቢሮ በመሆን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

እድሳቱ 20 ሚሊዮን ዩሮ የሚፈጅ ሲሆን ስራው ሲጠናቀቅ ቤተመንግስቱ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆንና ከፊት ለፊቱ በሚገኝ ስፍራም መናፈሻ እንደሚሰራ ተገልጿል።

ቀሪው 8 ሚሊዮን ዩሮ እ.አ.አ በ2021 ቀሪ ስራው ይፋ ሲደረግ በኤጀንሲው በኩል ይለቀቃል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ምርጥ የተባለ ዓለም አቀፍ ልምድን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በፈረንሳዊያንና ሌሎች ባለሙያዎች ይከናወናል ተብሏል።

የአገሪቷን ቅርስ በመጠበቅና በማስተዳደር ልምድ እንደሚቀሰምበት፣ በመዲናዋ አዲስ የቱሪስት መዳረሻ ልማት መገንባትና የቤተ መንግስቱን ታሪክ ለነዋሪው ማሳወቅ እንደሚያስችልም ተገልጿል።

የእድሳት ስራውን የቤተመንግስቱ አስተዳደር ከፈረንሳዊያን ባለሙያዎች ጋር በመሆን እንደሚቆጣጠረው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም