የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርኮችን ከሰደድ እሳት ለመታደግ የሚያስችል የእሳት ቁጥጥርና አስተዳደር ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርኮችን ከሰደድ እሳት ለመታደግ የሚያስችል የእሳት ቁጥጥርና አስተዳደር ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ፣ሃምሌ 10/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርኮችን ከሰደድ እሳት ለመታደግ የሚያስችል የእሳት ቁጥጥር እና አስተዳደር ስትራቴጂ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ፓርኮች ውስጥ በተለያየ ጊዜ የሚከሰተው ሰደድ እሳት የሚያደርሰው ውድመት ከፍ ያለ ነው።
በአገሪቱ ደጋማ እና ቆላማ አካባቢዎች በሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች በየአመቱ ሰደድ እሳት ስለሚቀሰቀስ በደን፣ በአዕዋፋትና በዱር እንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱ እየተለመደ መጥቷል።
የሰሜን፣ የባሌና አርሲ ተራሮች፣ የሃላይደጌ አሰቦት፣ የማጎ፣ የኦሞ እንዲሁም የጋምቤላና የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ፓርኮች ከዚህ ቀደም ሰደድ እሳት ከተቀሰቀሰባቸው መካከል ይገኙበታል።
በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ሰደድ እሳት መነሻ መንስዔ ለማወቅ ጥናት ሲደረግ መቆየቱን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ገልጿል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በጥናት ማየት እንደተቻለው የሰደድ እሳቱ መንስዔ አብዛኛው ሰው ሰራሽ ነው።
በተለይም የማሳ ዝግጅትና አዲስ የግጦሽ ሳር ለማብቀል የሚደረገው እንቅስቃሴ ችግሩን እያስከተለ እንደሆነ አመልክተዋል።
የሰደድ እሳቱ በዱር እንስሳት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት አስቀድሞ ለመከላከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለዚህም በፓርኮቹ ላይ የሚከሰት የሰደድ እሳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስትራቴጂ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ለቃፍታ ሽራሮ፣ ለሰሜንና ለባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች እንዲሁም ለሌሎችም ተጋላጭ ፓርኮች የእሳት ቁጥጥር እና አስተዳደር ስትራቴጂ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
ስትራቴጂው የሰደድ እሳቱን አስቀድሞ ከመከላከል ባሻገር ከተከሰተ ደግሞ ቶሎ ለመቆጣጠር እና የተጎዳውን ክፍል በፍጥነት እንዲያገግም ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።