አገርን ለከፋ ችግር በሚያጋልጥ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የመገናኛ ብዙሃንን የማስታመሙና የማስተማሩ ስራ ዋጋ አስከፍሏል-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
አገርን ለከፋ ችግር በሚያጋልጥ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የመገናኛ ብዙሃንን የማስታመሙና የማስተማሩ ስራ ዋጋ አስከፍሏል-ምሁራን
አዲስ አበባ፣ሐምሌ 10/2012 (ኢዜአ) አገርን ለከፋ ችግር በሚያጋልጥ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የመገናኛ ብዙሃንን የማስታመሙና የማስተማሩ ስራ ዋጋ ማስከፈሉን ምሁራን ተናገሩ። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በበኩሉ የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
በአገሪቱ በብሔር የተደራጁ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሲያስተላልፉ በነበሩት አፍራሽ ዘገባ ተገቢው እርምጃና እርምት ባለመወሰዱ አገርን ለከፋ ጉዳት ዳርጓል ይላሉ ምሁራኑ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ''የመገናኛ ብዙሃን ዘገባና ወቅታዊው ሁኔታ'' በሚል ከምሁራንና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት አካሂዷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ሙላት አለማየሁ እንዳሉት በአገሪቱ በብሔር የተደራጁ መገናኛ ብዙሃን ከጥቅማቸው ይልቅ ስጋታቸው ከፍተኛ መሆኑ በጥናት ተለይቷል።
የብሔር መገናኛ ብዙሃን አደረጃጃት በራሱ ችግር የሌለው ቢሆንም የተሰጣቸውን ነጻነት በአግባቡ ባለመጠቀማቸው ለአገር ስጋት ሆናዋል ነው ያሉት።
በአገሪቱ በአብዛኛው ብሔር ተኮር አደረጃጃት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን "ብሶት የወለዳቸው፣ የኔ ብሔር ተጎድቷል የሚል እሳቤን የያዙና የመገናኛ ብዙሃኑ ባለቤቶች ፍላጎት የተጫናቸው ናቸው" ብለዋል።
የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ብዝሃነትን የማያስተናግዱ የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት የሚፈልጓቸውን መገናኛ ብዙሃን የመጠቀምና ሌሎችን የመዘንጋት ሁኔታ ታይቶባቸዋልም ነው ያሉት።
በዚህ ሳቢያ የጥላቻ ንግግሮችን በማስተላለፍ ለጦርነትና የአገርን ህልውና የሚፈታተኑ ተግባራት ለመፈጸም ሲሰሩ ተስተውለዋል ነው ያሉት።
እንደዚህ ዓይነት አደረጃጀቶች በአግባቡ ካልተመሩ ለአገር ህልውና ከፍተኛ ስጋት መሆናቸውን አለማቀፍ ተሞክሮዎች ያሳያሉ ብለዋል።
በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በሚተላለፉ የተዛቡ ዘገባዎች ህዝቡን ለከፋ ጉዳት ያልዳረገው የህብረተሰቡ የመቻቻልና የመከባበር ባህል መሆኑን አስረድተዋል።
የህግና አስተዳደር ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ አሮን ደጎል በበኩላቸው አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን እንደ አገር የተሰጠውን የነጻነት ገደብ አልፈዋል ይላሉ።
የብሮድካስት አዋጁ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ ዘገባዎች፣ ጦርነት የሚቀሰቅሱ፣ የግለሰብን ሰብዓዊ መብት የሚነኩና በአገር መከላከያ ላይ የሚተላለፉ መረጃዎች ፈቃዱን እንደሚያሳግዱት ጭምር ነው የሚያነሱት።
በህጉ መሰረት መገናኛ ብዙሃን ባስተላለፉት ዘገባ ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶች በማስረጃ ከተረጋገጠ ባለቤቱ ካሳ እንደሚከፍል ህጉ ያስቀምጣል።
ነገር ግን የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፈትና የመገናኛ ብዙሃንን ነጻነት ለማረጋገጥ የተሄደበት መንገድ አገሪቱን ዋጋ አስከፍሏታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካሰት ባለስልጣንን ወክለው የተገኙት አቶ አብዩ መኮንንም ዴሞክራሲን ለማለማመድ ሲባል የመገናኛ ብዙሃን ያልተገባ ተግባር ሲያከናውኑ በማስታመምና በማስተማር መታለፉ አገርን ዋጋ አስከፍሏል የሚለውን ሀሳብ ይጋሩታል።
ነገር ግን ከስነ ምግባር ወጣ ያሉ መገናኛ ብዙሃንን በማስተማር፣ ማስጠንቀቂያ በመጻፍና ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለመመለስ ጥረት መደረጉን አልሸሸጉም።
ይሁንና አካሄዱ የአገርን ህልውና የሚፈታተን ተግባር በማምጣቱ ባለስልጣኑ የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በተጨማሪም አሰራሮች በአዋጅና በፖሊሲ እንዲደገፉ የማድረጉም ስራ ይቀጥላል ብለዋል።
ምሁራኑ መንግስት ህግ እንዲያስከብር የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ደግሞ የተሰጣቸው ነጻነት በአግባቡ እንዲጠቀሙና ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መክረዋል።