ከወጪ ንግድ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 10/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በ2012 በጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ2012 በጀት አመት የወጪ ንግድ አፈጻጸምን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የሚኒስቴሩ ንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንደተናገሩት በበጀት     

ዓመቱ በዘርፉ ከተያዘው ዕቅድ 80 በመቶው ተሳክቷል።

አፈጻጸሙ ከ2011 በጀት ዓመት ከተገኘው 2 ነጥብ 67 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር የ14 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።

የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር፣ የኮሮና ቫይረስ በምጣኔ ሃብቱ ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቋቋም በወጪ ንግድ ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች፣የውል ምዝገባና አስተዳደር ሥርዓት መመሪያ ተግባራዊ መሆን አፈጻጸሙን የተሻለ እንዲሆን አድርገውታል ብለዋል።

የተጠናቀው በጀት ዓመት ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘበትም ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ የግብርናው ዘርፍ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት የገቢውን 77 በመቶ ድርሻ ይዟል።

የማምረቻው ዘርፍ 406 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የማዕድን ዘርፍ 208 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝተዋል።

በንግዱ ቡና፣ አበባ፣ የቅባት እህል፣ ጫት፣ ጥራጥሬና ሰብልና ወርቅ 80 በመቶ ድርሻ እንዳላቸውም አምባሳደር ምስጋኑ አብራርተዋል።

ወርቅ፣ አበባ፣ ቡና፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት እንዲሁም መጠጥና ፋርማሲቲካል ከፍተኛ የገቢ እድገት አስመዝግበዋል ብለዋል።

ገቢውን ለማሳደግ በአዲሱ በጀት ዓመት አዳዲስ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንደሚገቡ ተናግረዋል።

በመሆኑም ምርት በክምችት የያዙ አቅራቢዎች እስከ መስከረም 30 ቀን 2013 ድረስ ለገበያ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

ከሐምሌ 15 ቀን 2012 ጀምሮ አቀናባሪዎች የአኩሪ አተር ምርትን ከልዩ የግብይት መድረክ ብቻ እንዲገዙ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።

ምርቱን በሕገ ወጥ መንገድ ገዝተው በክምችት የያዙ የግብይት ተዋናዮች እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2012 ድረስ ብቻ በልዩ ሁኔታ የያዙትን ምርት በአቅራቢዎች በኩል ወደ ምርት ገበያው እንዲያስገቡ ውሳኔ መተላለፉን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስገዳጅ የሆኑ ከቡና ውጪ ምርቶችን የሚልኩ ነጋዴዎች በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ቀርበው ኦዲት አንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

ሕገወጥ ንግድን ከመቆጣጠር አንጻር ምርት አከማችተው በወቅቱ ያላወጡና ምርት ያባከኑ 10 ላኪዎች ንግድ ፈቃዳቸው መሰረዙንና በሕገ ወጥ መንገድ ምርት ወደ ውጭ የላኩ 59 ላኪዎች ለሦስት ወራት የንግድ ፈቃዳቸው መታገዱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም