ፈንዱ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ፈንዱ 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰበሰበ
አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገለጸ።
ገቢው ከነዳጅ ፣ ከዘይትና ቅባት ከተጣለ ታሪፍ፣ ከመንገድ ጠቀሜታ ታሪፍ ፣ ከግምጃ ቤት ሰነድ ከሚገኝ ወለድና ክብደትን መሠረት ካደረገ ዓመታዊ ተሽከርካሪ ማደሻ ክፍያ መገኘቱን አስታውቋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ የዕቅዱን 91 በመቶ ማሳካቱንም አመልክቷል።
ጽህፈት ቤቱ ካገኘው ዓመታዊ ገቢ ለመንገድ ደህንነት ጥገናና ደህንነት የሚውል ለፌዴራልና ለክልል መንገድ ኤጀንሲዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አመልክቷል።
ጽህፈት ቤቱ በጀት ዓመት 14 ሺህ 532 ኪሎ ሜትር መንገድ መጠገኑንም ገልጿል።
የመንገድ ጥገናውን ውጤታማ ለማድረግ ከስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር መሥራት ጀምሬያለሁ ብሏል።
የኤጀንሲዎችን አቅም ለመገንባት በ600 ሚሊዮን ብር ወጪ ለጥገና የሚያገለግል መሣሪያ መግዛቱን ጽህፈት ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።