የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ በማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በሚፈጸም ስርቆትና ውድመት ጫና ደርሶበታል - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ በማስተላለፊያ መስመሮች ላይ በሚፈጸም ስርቆትና ውድመት ጫና ደርሶበታል
አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የሚፈጸመው ስርቆትና ውድመት በአቅርቦቱ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው አለ።
ኅብረተሰቡ በመስመሮቹ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት እንዲከላከልም ጥሪ አቅርቧል።
ተቋሙ በክረምቱ ወራት የኃይል ብልሽትና መቋረጥ ቢያጋጥም ከወትሮው በተሻለ መጠገን የሚስችለውን ዝግጅት ማድረጉንም ገልጿል።
ከጥገና በተጨማሪም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት እየሰራሁ ነው ብሏል።
በኢትዮጵ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ለኅብረተሰቡ የተሟላ አገልግሎት ለማቅረብ በመስመሮች ላይ የሚደርሱ ስርቆቶችና ውድመት ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠሩ መሆኑን አመልክተዋል።
በመላ አገሪቷ የሚያጋጥመውን የኃይል መቆራረጥ ዜሮ ማድረስ ባይቻልም ችግሩን መቀነስ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነውም ብለዋል።
ኅብረተሰቡ በመስመሮቹ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ሕገ-ወጥ ተግባራት ከመከላከል ባሻገር ኃይል ቆጣቢ የኤሌክትሪክ መሳሪያዎችን እንዲጠቀምም አሳስበዋል።
ገበያ ላይ የሚሸጡ ከፍተኛ ኃይል የሚወስዱ የኤሌክትሪክ እቃዎች ኅብረተሰቡን ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረጋቸውም በላይ ለኃይል መቆራረጥ ምክንያት እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።
ተቋሙ ያረጁ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን በመቀየር የተሻለ አግልግሎት ለማቅረብ እየሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ ደንና ጫካዎችን አልፈው የሚሄዱ የማስተላለፊያ መስመሮችን መስመሮችን እንደ ራሱ ሃብትና ንብረት እንዲንከባከብና እንዲጠብቃቸውም ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ 56 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደማያገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ።