የመገኛ ብዙኃን የኮቪድ 19 መረጃ ከዕለታዊ ሪፖርት የተሻገረ መሆን ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
የመገኛ ብዙኃን የኮቪድ 19 መረጃ ከዕለታዊ ሪፖርት የተሻገረ መሆን ይጠበቅበታል
አዲስ አበባ ሀምሌ 10/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የኮቪድ 19 መረጃ ከዕለታዊ ሪፖርት ባለፈ የግለሰቦችን ታሪክ በማስተማሪያነት ማቅረብ እንደሚገባቸው በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ባለሙያ አመለከቱ።
ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው ኮቪድ-19 የምድራችን ስጋት ሆኖ መቀጠሉ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያመለክታል።ከ13ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤የሟቾችም ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን ልቋል።
በኢትዮጵያም የስርጭት መጠኑ በፍጥነት እየጨመረ መጥቶ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ8 ሺህ በላይ ደርሷል።150 ሰዎችም ሞተዋል።
የአዲስ አበባ የጋዜጠኝነት ኮሙኒኬሽን መምህር ዶክተር ተሻገር ሽፈራው እንደሚገልጹት የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ቫይረሱ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለማሳየት የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች አቀራረብ መቀየር ይጠበቅባቸዋል።
መገናኛ ብዙኃኑ በየቀኑ የሚያቀርቡት መረጃ በቫይረሱ የተያዙትን፣የሞቱትንና ያገገሙትን ከመግለጽ የዘለለ አይደለም ያሉት ምሁሩ፤ይህም መረጃ ከመስጠት ያላለፈና አስተማሪነቱም አነስተኛ ነው ብለዋል።
ቫይረሱን አስመልክቶ አብዛኛው ኅብረተሰብ ግንዛቤ ቢጨብጥም፤አሁን ከሚታየው መዘናጋት በመውጣት ጥንቃቄን እንዲለምድ የአቀራረብ ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በየዕለቱ እየተሰጠ ያለው የቁጥር መረጃ ጠቃሚ ቢሆንም፤ ሰዎች ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውንና ሌሎችን ከበሽታው ለመጠበቅ በሚያደርጉት ጥንቃቄ ላይ ለውጥ እንዲያመጣ መደረግ አለበት ይላሉ።
ሰዎች በአብዛኛው የሚማሩት በተነገራቸው ሳይሆን በተጨባጭ ባዩት በመሆኑ በኮቪድ 19 ላይ የሚቀርቡት ዘገባዎች በዚህ መልክ መቃኘት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
ዶክተር ተሻገር እንደሚሉት የግለሰብ ታሪኮችን በዜናና በፕሮግራሞች በማቅረብ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲጨብጥና የባህርይ ለውጥ ለማምጣት ይቻላል።
በተለይም በቫይረሱ ተይዘው ያገገሙ ሰዎችን ታሪክ በማጋራት፣በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጀርባ የነበሩ ሰዎችን በማወያየትና የተለየ ታሪክ ያላቸውን ሰዎች በማቅረብ ማስተማር ይገባል ብለዋል።
የሴተኛ አዳሪዎች፣ የህጻናትና ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን ታሪክ ከራሳቸው ሕይወት ተነስቶ በማሳየት ኅብረተሰቡ እንዲማርበትና እንዲጠነቀቅ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑንም ዶክተር ተሻገር አመልክተዋል።
ይህም መንግሥት ቫይረሱ በኢኮኖሚያዊ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ መስኮች እያደረሰ ያለውን ጉዳት በምሁራን ለማስተንተንና መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለማከናወን እንደሚረዳው አስረድተዋል።
መገናኛ ብዙኃን ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ግለሰቦቹና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት መተባበር እንደሚገባቸው ምሀሩ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሳይካትሪ ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት አሰፋ በበኩላቸው የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተሰማ በኋላ በማሳወቅና በማስተማር ሚናቸው የላቀ እንደነበር ገልጸዋል።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከሚታየው መዘናጋት ለመውጣት ሚናቸውን ቀጣይነት ባለውና የባህርይ ለውጥ በሚያመጣ መልኩ መቃኘት ይገባቸዋል ብለዋል።
ዜጎች ቤት መቀመጥንና የለይቶ ማቆያ ማዕከላትን ምንነት ለይተው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ይገባል ያሉት ዶክተር ዳዊት፤ከኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ታሪክ በማጋራት ማስተማር ይገባል ይላሉ።
ዜጎች ከቀደመው ማህበራዊ አኗኗራቸው ተገድበው ራሳቸውን ለይተው በቤት በመቀመጥ ያገኙትን መልካም ተሞክሮ ማቅረብ ጠቃሚነት እንዳለውም አስረድተዋል።
በዚህም በተለይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከሚደርስባቸው የሥነ ልቡና ጫና እንደሚያላቅቃቸው ተናግረዋል።