ቀጥታ፡

በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ለትራንስፖርት ዘርፍ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ ሀምሌ 9/2012(ኢዜአ) በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ሰፋፊ የትራንስፖርት ዘርፍ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በትኩረት ለማከናወን መታቀዱን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትራንስፖርት ዘርፍ የሥስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ላይ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ወቅት መሪ ዕቅዱን ያቀረቡት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዘርፉ በርካታ ሥራዎች የተሰሩ ቢሆንም አሁንም የሚቀሩ ተግባራት እንዳሉ ገልጸዋል።

የትራንስፖርት ዘርፍ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የአገልግሎት ዘርፉን አጣምሮ የሚሰራ መሆኑን ሚኒስተሯ ጠቁመዋል።

እስካሁንም በአየር ማረፊያ ግንባታ ዘርፍ 22 አየር ማረፊያዎች፣ ዘጠኝ ጥርጊያ አየር ማረፊያዎችና አራት ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

''በመንገድ ልማት ዘርፍም ከ19 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ተዘርግቷል'' ያሉት ሚኒስትሯ፣ በባቡር መስመርም ጅማሮዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት አሁን ያሉትን መነሻዎች በመጠቀም በተለይ የመሰረተ ልማት ዘርጋታ ሥራ በስፋት እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

በዚህም የመንገድ ሽፋኑን አሁን ካለበት ወደ 225 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ በመሪ ዕቀዱ ላይ መቀመጡን ነው የገለጹት።

የባቡር መሰረተ ልማቱን አሁን ካለበት 902 ኪሎ ሜትር በአጠቃላይ ወደ 3 ሺህ 999 ኪሎ ሜትር ለማድረስ ውጥን እንደለም አብራርተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የደረቅ ወደቦችን ማስፋት፣ የሞተር አልባ ትራንስፖርትን ማሳደግ፣ የኬብል ታክሲ መጀመርና ሌሎች የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሻሉ ዕቅዶች መኖራቸውን ገልዋል።

"ዕቅዱን ወደ ውጤት ለመቀየር በዘርፉ ያለው የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም እንዲያድግ ይደረጋል" ነው ያሉት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት።

''ዕቅዶቹ የታሰበውን ያህል ውጤት እንዲያስገኙ በየዓመቱ ቢከለሱና ቢፈተሹ የተሻለ ይሆናል'' ያሉት ደግሞ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ምሁሩ ዶክተር ማቲዎስ ኢንሰርሙ ናቸው።

በአጠቃላይ መሰረተ ልማት ላይ ትኩረት ማድረጉ የተሻለ መሆኑን የሚመክሩት ዶክተር ማቲዎስ፣ በተለይ ለባቡር መሰረተልማት ልዩ ትኩረት ያሻል ብለዋል።

የባቡር መስመር በአራቱም የአገሪቷ አቅጣጫዎች ቢዘረጋ የሎጆስቲክስ ዘርፉን በተሻለ መልኩ ውጤታማ ያደርገዋል የሚል ዕምነትም አላቸው።

ሌላው የመሰረተ ልማት ዘርፍ ምሁር የሆኑት ዶክተር ኢሳያስ ገብረጊዮርጊስ ደግሞ መሰረተ ልማት ከመዘርጋት በሻገር በትክክል ማሰተዳደር ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

''መሰረተ ልማት በአግባቡ ከተያዘ ውጤታማና ጠቃሚ ሲሆን በአግባቡ ካልተያዘ ግን በቀጣዩ ትውልድ ላይ ጫና ይፈጥራል'' ብለዋል።

የግል ዘርፉን ወክለው በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ወይዘሮ ኤልሳቤት ጌታሁን ደግሞ " ዘርፉን ትልቁ የውጪ ምንዛሬ ማግኛ ማድረግ ያስፈልጋል" ይላሉ።

"በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመጠቀም አገሪቷን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማዕከል ማድረግ ይቻላል" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ጉዳይ በዕቅዱ ውስጥ በአግባቡ ሊታይ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በፕላንና ልማት ኮሚሽን አስተባባሪነት የዘርፎች የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ውይይት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም