ኢትዮጵያዊያን በሕዳሴው ግድብ ላይ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት ዓለም አቀፍ መርሃ ግብር ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን በሕዳሴው ግድብ ላይ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት ዓለም አቀፍ መርሃ ግብር ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ ሀምሌ 9/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በተመሳሳይ ሰዓት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ድምጻቸውን የሚያሰሙበት ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው መርሃ ግብር ሊካሄድ ነው ተባለ።
ሊፍት ኢትዮጵያ የተባለ አገር በቀል የግብረሰናይ ድርጅትና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት መርሃ ግብሩን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የመርሃ ግብሩ ዓላማ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን "ድምጻችን ለግድባችን" በሚል መሪ ሀሳብ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላቸውን አቋም የሚያንጸባርቁበት መድረክ መፍጠር ነው።
የሊፍት ኢትዮጵያ አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሪት ዘኢማ አህመድ "ዝግጅቱ ለ20 ደቂቃ የሚቆይ ነው፤ ዜጎች በተመሳሳይ ሰዓት በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ድምጻቸውን ያሰማሉ" ብለዋል።
በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች መርሃግብሩን አስመልክቶ የንቅናቄና የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
ዜጎች ለግድቡ ያላቸውን ድጋፍ በዕለቱ በምን አይነት መልኩ በመግለጽ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚችሉ የገለጹት ደግሞ የሊፍት ኢትዮጵያ አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት የቦርድ አባል አቶ አብርሃም ስዩም ናቸው።
መርሃግብሩ መቼ እንደሚካሄድና በዕለቱ የሚከናወኑ ዝርዝር ተግባራት በቀጣይ ጊዜ እንደሚገለጹም አመልክተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር በበኩላቸው፣ በዝግጅቱ ድምጽን ከማሰማት ባለፈ የቦንድ ግዢ መርሃ ግብር እንደሚኖር ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና ኤምባሲዎች መርሃግብሩ ውጤታማ እንዲሆን ከሁለቱ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 74 ንጥብ 5 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ግድቡ ውሃ መያዝ የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
በተያዘው ወርም 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ መያዝ ይጀምራል።