ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ

ሀዋሳ ሐምሌ 09/2012  (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 11 ወራት ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን በክልሉ የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ገለጸ፡፡ 

የአባይ ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ ባጋጠመው ችግር ድጋፉ ተቀዛቅዞ የነበረው ከለውጡ ወዲህ መንግስት ያደረገው  የማሻሻያ ስራ  የህዝቡን አመለካከት ወደነበረበት መመለስ የቻለ ነው፡፡

የምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሚልክያስ እስራኤል እንደተናገሩት ግብጽና ሌሎች አፍራሽ ኃይሎች የሚያሰራጩትን የሀሰት  መረጃ ወደ ጎን በመተው የክልሉ ነዋሪ ህዝብ የሚያደርጉት ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚህም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት  እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ ከ52 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብስቡን ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ በአጠቃላይ ከአንድ ቢሊዮን 500 ሚሊዮን ብር በላይ ክልሉ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለግድቡ  ግንባታ ድጋፍ  አጠናክሮ መቀጠሉንና በተለይ የ8100 ዕጣው የክልሉን ነዋሪ የተለየ ንቅናቄ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲስ ቦንድ ሽያጭ፣ የቦንድ ክፍያ  ጊዜ የደረሰን ማራዘም እና የዓይነት ስጦታዎች ጨምሮ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮች መዘርጋቱን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

እስከ ግድቡ ግንባታ ፍጻሜም  ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ደጋፍ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የህዳሴው ግድብ በእኛ ጊዜ ትውልዱና መንግስት በያዙት ቁርጠኛ አቋም እየተገነባ ያለ የህዝብ ሃብት ነው ያሉት ደግሞ በደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክተር  አቶ ጫኔ አሰፋ ናቸው።

ኢትዮጵያ በራሷ ህዝብ አቅም ግድቡን መስራት መቻሏ አፍሪካዊያን በራሳቸው ታላላቅ ፕሮጄክት ማሳካት እንደሚችሉ ተምሳሌት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ከግብጽ በበለጠ አሜሪካን፣አውሮፓዊያንና መላውን ዓለም  የሚያስደነቅ አኩሪ ተግባር ነው።

አቶ ጫኔ ግድቡን እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን የሚለውን በተግባር የሚናሳየው እንጂ ዝም ብሎ መፈክር አይደለም  ብልዋል፡፡

ግንባታው ከተጀመረ አንስቶ ሳያቋርጡ ቦንድ በመግዛትና በ8100 ዕጣ  እየተሳተፉ እንደሚገኙ አመልክተው  እስከሚጠናቀቅም ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ግድቡን ማጠናቀቅ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የሞት ሽረት ወይም ከድህነት የመላቀቅና ያለመላቀቅ በመሆኑ ጠላቶቻችን አይሳካለቸውም ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት  አቶ አማኑኤል ጳውሎስ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ መምህራን ከደመወዛቸውና ተማሪዎች ለሻይ ቡና ከሚይዙት ቦንድ በመግዛት በግንባር ቀደምትነት የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለያየ መልኩ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚሰነዘሩ ያልተገቡ ትንኮሳዎችን የግድቡን ግንባታ ሂደት ለማስተጓጎል ነው ያሉት አቶ አማኑኤል ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሴክተሩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

ግንባታውን ለማደናቀፍ  የሚነዙ  ውዥንብሮችን ወደጎን በመተው የሃገሪቱን  ልማት ለማፋጠን በአንድነት መረባረብ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ዳንኤል ሞርካ በሰጡት አስተያየት የግድቡ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠ በኋላ  ባለማቋረጥ ቦንድ በመግዛት እየተሳተፍኩ ነው ብለዋል።

በሰሞኑ ታዋቂው አርቲስት ሃጫሉን በመግደል ሃገርን ለማተራመስ የተደረገው ሙከራ ግንባታውን ለማደናቅፍ  የተደረገ ሴራ መሆኑን አስታውሰው  የኢትዮጵያ ህዝብ ወትሮም ለጠላት እጅ እንደማይሰጥና እሳቸውም  እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸው እንደማይቋርጡ ገልጸዋል፡፡

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም  የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠው  ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላይ 74 በመቶ  መድረሱን በቅርቡ መገለጹ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም