ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው ድርድር ይቀጥላል

አዲስ አበባ  ሀምሌ 9/2012 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው ድርድር ቀጣይነት እንደሚኖረው የውሃ፣ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።

ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በሰጡት መግለጫ በግድቡ ዙሪያ በሚደረግ ድርድር የታችኛው ተፋሰስ አገራት ከህግ ማዕቀፍ አንጻር አሳሪ አንቀጽ ለማስገባት የሚያደርጉት ጥረት ለ11 ቀናት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ያለ ስምምነት እንዲጠናቀቅ አድርጓል። ይሁንና ቀጣይነት እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

"በድርድሩ ይዘን የምንቀርበው ሀሳብ የዛሬውም ቀጣዩም ትውልድ ውሃ መጠቀም የሚያስችለው መብት ተገቢ ባልሆነ አንቀፅ እንዳይታሰር የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

ድርድሩ ጥንቃቄ እና ብስለት በተሞላበት መንገድ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

ይህ እየተደረገ ያለው ኢትዮጵያ እየለማች እና እየበለፀገች በምትሄድበት ወቅት የግድቡ አጠቃቀም ላይ የማሻሻያ ህጎች በማስፈለጋቸው ነው ብለዋል።

በግድቡ አሞላል፣ በግድቡ ደህንነት እና መረጃ ልውውጥ ግልፅ እንደሆነና በአንዳንድ የህግ ማዕቀፎች ላይ ስምምነት እንዳልተደረሰ ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ  በተጠና መልኩ የሚካሄድ ስለሆን የውሃ ሙሌት እና የግድቡ ግንባታ አብሮ የሚከናወን ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የግድቡ ውሃ ሙሌት  የማንንም ፈቃደኝነት እንደማይጠይቅና የድርድሩ አካል አለመሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም