ቀጥታ፡

የግብጽ ስጋት ውሃ ሳይሆን ቀጠናዊ የባላይነት ተጽዕኖ እነጠቃለሁ የሚል ነው - ምሁራን

አዳማ (ኢዜአ) ሐምሌ 8/2012 )ግብጽን የሚያሳስባት የውሃ ጉዳይ ሳይሆን ያላትን ቀጠናዊ የኢኮኖሚ የበላይነት ተፅዕኖ በኢትዮጵያ እነጠቃለሁ በሚል ስጋት መሆኑን በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ዘርፍ ምሁራን ገለጹ።

ግብጽ ኢትዮጵያ ግደቡን ገንብታ ካጠናቀቀች በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ እድገቷና ልማቷ ስለሚፋጠን በቀጣይነት በቀጠናው ላይ ያላት የበላይነት በኢትዮጵያ ይያዝብኛል የሚል አዙሪት መሆኑንም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው የውሃ እና ኢንቫይሮሜንታል ኢንጂነሪንግ ምሁር ዶክተር ኬይረዲን ተማም ኢትዮጵያ ያላት ተሞክሮ የመቻቻልና አብሮነት ብሎም የጋራ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ እንጂ ግብጽን የሚጎዳ አይደለም ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤትም ሆነ ከሌላው የዓለም ሀገራት በኃይማኖት የመጋጨትም ሆነ በኢኮኖሚ ተጋጭታ አታውቅም ያሉት ምሁሩ፤ ድንበሯን አልፎ የሚመጣን ማስተናገዱን ግን እንደሚትችልበት አጉልቶ ማሳየት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ምሁራንና ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያ በወንድማማችነት፣ ፍትሐዊና እኩልነት ላይ የተመሰረተ የውሃ ሀብት ከፍፍል ተግባራዊ በማድረግ ግድቡን እየገነባች መሆኑን አጉልተን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ለግብጾች ማስረዳት ይጠበቅብናል ብለዋል።

 ሁሉም ዜጋ የኢትዮጵያን ማንነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየትና ማሳወቅ እንደሚጠበቅበት ያመለከቱት ምሁሩ ፤ ግብጽ እያረመደች ያለችው የጥፋት ኃይሎች ዓላማ እንዲገታ ሁሉም የዜግነት ግዴታውን በመወጣት የጋራ የሆነውን ፕሮጀክታችንን ማሳካት እንደሚገባ ተናግረዋል።

 ምሁሩ እንዳብራሩት ስለግድቡ አፍራሽ ተግባር የሚያራምዱ ኃይሎች ከማህበረሰቡ ጋር መኖር የማይችሉ ከመሆኑም ባለፈ ግድቡን በማሳካቱ ላይ ዳያስፖራም ሆነ የሀገር ውስጥ ዜጎች በአንድነት ሆነው ተፅዕኖ ማሳደር መቻል አለባቸው።

የግድቡ ዓላማ ኃይል ማመንጨት ነው፤ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ውሃውን መልቀቅ አለባት፤ ውሃ መልቀቁን ግድቡ ኃይል የማመንጨት ዓላማ ነው ብለዋል።

ግድቡ ድንበር ላይ ተጠግቶ የተገነባውም የግርጌ ሀገራት በተለይም ግብጽና ሱዳን የውሃ መጠኑ እንዳያንስባቸውና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጭምር እንደሆነም ዶክተር ኬይረዲን ተናግረዋል።

 የግብጽ ሽኩቻና የሀገር ውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎች ሴራ የጋራና ብሔራዊ ጥቅም ለማሳጣት እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል ዲን ዶክተር ዓለሙ ጎንፋ ናቸው።

 በዓባይ ግድብ ላይ ፖለቲካ መስራት አይቻልም፤ ግድቡንም መሸጥም ሆነ መግዛት አይቻልም፤ ከግለሰቦቹም ሆነ ከቡድኑ ሊገዛ የሚችልም ኃይል ሃብቱ የኢትዮጵያ ህዝብ በመሆኑ ውጤታማ አይሆንም" ብለዋል።

 በዚህም የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያ ዜጎች ጥቅም፣ ኑሮና ህይወት ብሎም የህልውና ጉዳይ በመሆኑ መንግስት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ህዝብ በጋራ በመሆን ግንባታውን ከግብ ማድረስ አለብን ብለዋል።

በውስጣችን ጉዳይ በመግባት በተለይም መንግስት ተረጋግቶ የግድቡን ግንባታ ከዳር እንዳያደርስና የውሃ ሙሌቱ እንዳይሳካ ግብጽ እየሰራች መሆኑን እንደሚገነዘቡ ገልጸዋል።

 በዚህም የኢትዮጵያ ምሁራን ፣ ህዝብ፣ ምሁራኑ፣ ተፎካካሪ ፓርቲው በአንድነት ሆነው ይኸን በሀገር ጥቅም ላይ የተደቀነውን አደጋ ማክሸፍ የጋራ ኃላፊነታችን ሊሆን ይገባል ብለዋል።

 ዓባይ ከኪሳችን አውጥተን መስራታችን ብቻ የእኛ አያደርገውም ፤ የራሳችን መሆን የሚችለው ማንም ኃይል ግድቡን ማስቆም እንደማይችል ግብጽን ማሳመንና ከሴራዋ ማስቆም ሲቻል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ግድቡ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት ከጀመረ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅሟን በመገንባት የዜጎቿን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኑሮ ለመለወጥ እየሰራችበት ያለ መሆኑን ለግብጽም ሆነ ህዝቦቿ ማሳመን የምንችለው አንድነታችንን አጠናክረን መቀጠል ስንችል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም