ሰላምን የሚያውኩ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደረገው ክትትል መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን የሚያውኩ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደረገው ክትትል መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ
ጅማ ሐምሌ 8/2012 (ኢዜአ) የጋዜጠኝነት የሙያ ስነምግባርን በጣሰ መልክ የሃገርን ሰላምና የህዝቦችን አብሮነት ለማወክ የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃንን በመከታተል አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ተመለከተ።
በወቅታዊ ጉዳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ጥናት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተው ጌታቸው ጥላሁን እንደገለጹት መገናኛ ብዙሃን የሚያስተላለፉት መረጃ ማህበረሰቡ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖ አብሮ ማየትና ማሰብ አለባቸው።
ለዚህም ትልቁ ጉዳይ የጋዜጠኝነት የሙያ ስነ-ምግባርን ማክበር እጅግ አስፈላጊ ነው።
"ዘርፉን የግልና ቡድንፍላጎትን ለማርካት የምንጠቀምበት ከሆነ ሙያውን እያረክስነው እናገለግለዋለን የምንለውን ማህበረሰብን ረስተነዋል ማለት ነው" ብለዋል
ይህ ሁኔታ መስተካከል አለበት ያሉት ዶክተር ጌታቸው ለዚህም የሙያውን ስነምግባር ጨምሮ ከሀገሪቱ ህገ መንግስት ጀምሮ ያሉትን ህግጋት ማስከበር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከሙያ ስነ ምግባር ባፈነገጠ አካሄድየሚተላለፈው ጉዳይ ታባብሶ ጥግ በመድረሱ የኢትዮጵያ ብርድካስት ባለስልጣንምአቅሙን ማሳየት ጀመረ እንጂ ችግሩ የቆየመሆኑን አውስተዋል።
"በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መገናኛ ብዙሃንን ማወያየት፣ ማነጋገር፣ ማከራከር እና ማቀራረብ ይጠበቅባቸዋል''ብለዋል።
አሁን ሀገራዊ አንድነት አደጋ ውስጥ የገባበት ጊዜ በመሆኑ መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነ ምግባራቸውን ጠብቀው ለህዝብና ለሀገር መስራት ይኖርባቸዋል።
ጽንፍ የረገጡጉዳዮችን ወደ ማዕከል ሊያመጣ የሚችል የውይይት ፣የክርክር፣ የንግግር መድረክ ያስፈልጋል ሲሉ ዶክተር ጌታቸው ተናግረዋል ።
ዶክተር ጌታቸው አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ግጭት አቀጣጣይ ከመሆን በመቆጠብ ዜጎች በነጻነትና በሰላም ወጥተው እንዲገቡ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ሙያዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ከዚህ አንጻር ሚዛናዊ ሆነው መድረክ እያመቻቹ በመስራት የሚደነቁ እንደመኖራቸው አንዳንድ ጽንፍ የረገጡ መገናኛ ብዙሃንም ስላሉ መታረም እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ለመሸርሸር የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃን ላይ መንግስት እርምጃ መውሰድ የሚያስችለውን መረጃ እየሰጠ መሆኑን ኢዜአ በቅርቡ ዘግቧል።