ማኅበሩ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የ100 ሺህ ብር ቦንድ ገዛ ማዕድም አጋራ - ኢዜአ አማርኛ
ማኅበሩ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ የ100 ሺህ ብር ቦንድ ገዛ ማዕድም አጋራ
ሐምሌ 8/2012 (ኢዜአ) የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የጋራዥ ዘርፍ ማኅበር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመቶ ሺህ ብር ቦንድ ሲገዛ ለአቅመ ደካሞችም ማዕድ አጋርቷል።
ማኅበሩ ድጋፉን ያደረገው ከክፍለ ከተማው ንግድ ቢሮ ጋር በመተባበር ሲሆን 30 ለሚሆኑ አቅመ ደካሞችና ሴቶች 38 ሺህ ብር የሚገመት የምግብ ቁሳቁስም አጋርተዋል።
የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፈቃዱ ካሳሁን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ብዙዎችን ለችግር በመዳረጉ የማኅበሩ ድጋፍ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የጋራዦች ዘርፍ ማኅበር ዋና ሰብሳቢ አቶ ዝናቡ መንገሻም "በአገሪቷ በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ የተጎዱ አቅመ-ደካሞችን ማዕድ በማጋራት ከሕዝብና ከመንግስት ጋር ያለንን አጋርነት ለመግጽ ድጋፉን አድርገናል" ብለዋል።
ከማዕድ ማጋራት በተጨማሪም የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ቦንድ በጋራዥ ማኅበሩ ስም በስጦታ ማበርከታቸውንም ገልጸዋል።
ድጋፋቸው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት መሆኑ እስኪቀር እንደሚቀጥልም ነው የተናገሩት።
ማኅበሩ በቀጣይም የችግኝ መትከልና የደም ልገሳ ተግባራትን እንደሚያከናውን ገልጸዋል።