ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ከዓረቡ ዓለም ድጋፍ ለማግኘት በሃይማኖት ስም የምታሰራጨው መረጃ ታሪክን ይቃረናል - ምሑራን - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ከዓረቡ ዓለም ድጋፍ ለማግኘት በሃይማኖት ስም የምታሰራጨው መረጃ ታሪክን ይቃረናል - ምሑራን
ሐምሌ 8/2012 (ኢዜአ) ግብጽ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በተመለከተ ከዓረቡ ዓለም ድጋፍ ለማግኘት ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት በመሆኗ ሙስሊሞችን ትጨቁናለች በሚል የምታሰራጨው መረጃ ታሪክን ይቃረናል ሲሉ ምሑራን ገለጹ።
ኢትዮጵያዊያን ግብጽ ለምታሰራጨው የሐሰት ትርክት ጆሮ ሳይሰጡ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩም ምሑራኑ መክረዋል።
ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከጀመረች አንስቶ ግብጽ ግንባታው ለማሰናከል ያላንኳኳችው በር እንደሌለ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ ምሑራን ይገልጻሉ።
የምትቀይሰው ስትራቴጂ የግድቡን ስራ ማስቆም እንዳልቻለም ተናግረዋል።
ነገር ግን ግብጽ ከዓረቡ ዓለም ድጋፍ ለማግኘት ከምትነዛው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ መካከል ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት በመሆኗ ሙስሊሞች ይጨቆናሉ የሚል እንደሚገኝበት ምሑራኑ ያነሳሉ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓረብኛ ቋንቋ መምህርና የኢትዮጵያ እስልምና ታሪኮች ተመራማሪ ዕጩ ዶክተር ሃሰን መሃመድ "ግብጽ ለፖለቲካ ትርፍ ስትል ከታሪክ ጋር ግጭት ውስጥ ገብታለች" ይላሉ።
ኢትዮጵያ እስልምናን ጨምሮ የተለያዩ እምነቶችን ተቀብላ በእኩልነት በማስተናገድ ቀደምት አገር መሆኗን የታሪክ ድርሳናትን በማጣቀስም አብራርተዋል።
በእምነት ሽፋን ከዓረቡ ዓለም ድጋፍ በማግኘት የግድቡን ስራ ለማደናቀፍ ኢትዮጵያ ከእስልምና ጋር ያላትን ትስስር ማዛባት "ከታሪክ ጋር መጋጨት ነው"ም ብለዋል።
"ግብፅ የቅኝ ግዛት ውልን ከመተግበር ጀምሮ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ግድቡ እውን እንዳይሆን ከእውነት የራቁ መረጃዎችን በዓረብኛ ቋንቋ ከማሰራጨት ተቆጥባ አታውቅም" ብለዋል።
ፍትህ ባልሰፈነበት ወቅት የተፈረመ የቅኝ ግዛት ውልን ለመተግበር የምትቀይሳቸውን መንገዶችም በዚህ ዘመን የማይታሰቡ "ኋላ ቀር አካሄዶች" ሲሉ ገልጸውታል ተመራማሪው።
'የኢትዮ-ዓረብ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና የኢትዮጵያ ታሪክ በእስልምና ላይ' በሚል ከ30 በላይ የጥናት ግኝቶችን የሰሩት አጥኚና ተመራማሪ ዶክተር አደም ካሚል በበኩላቸው "ግብጽ ስለ ኢትዮጵያ የውሸት ፕሮፓጋንዳ መንዛት የኖረችበት ነው" ይላሉ።
ግብጽ የሕዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ለተፋሰሱ አገራት ከሚሰጠው የምጣኔ ሃብት፣ የማኅበራዊና ፖለቲካዊ ትስስር በተቃራኒው እንደምትጓዝም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ግድቡን ካጠናቀቀች በቀጣናው የሚኖራትን ተጽዕኖ ጠንቅቃ የምትረዳው ግብጽ የግድቡ እውን መሆን እንቅልፍ እንደነሳት ነው የተናገሩት።
የሃያላን አገራትን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የዓረቡን ዓለም በሮች እያንኳኳች ያለችው ግብጽ የግድቡ ውሃ ሙሌት እውን እንዳይሆን ቆርጣ ተነስታለች ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የግብጽ መገናኛ ብዙሃን "ኢትዮጵያዊያን አንድ አይደሉም በማለት አጀንዳ አድርገው እየሰበኩ በመሆኑ አንድነታችንን የምናጠናክርበት ጊዜ አሁን ነው" ብለዋል ዶክተር አደም።
ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለውን ትክክለኛውን እውነታ ለዓረቡ ዓለም ለማሳወቅ መገናኛ ብዙሃን በዓረብኛ ቋንቋ በሰፊው መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ ከመጡ ሃይማኖቶች እስልምናን እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ615 በመቀበልና በማስተናገድ እምነትን ለፖለቲካዊ ትርፍ ከምትጠቀመው ግብጽ በ24 ዓመት እንደምትቀድምም አብራርተዋል።