በህዳሴ ግድብ ላይ ሲደረግ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ሳይደረስ መጠናቀቁ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በህዳሴ ግድብ ላይ ሲደረግ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ሳይደረስ መጠናቀቁ ተገለጸ
አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2012 (ኢዜአ) በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ሳይደረስ መጠናቀቁን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ተናገሩ።
ባለፉት 11 ቀናት በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮችና ታዛቢዎች ሲካሄድ በነበረው ውይይት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ መግባባት ቢኖርም በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ሳይደረስ መጠናቀቁን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ዛሬ እንደተናገሩት እስከ ትናንት ሌሊት ድረስ የተካሄደው ድርድር የተጠናቀቀ ቢሆንም ማጠቃለያ ላይ አልተደረሰም።
በመሆኑም እንደገና ወደ መሪዎች እንደሚመለስና መሪዎቹ ተገናኝተው አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
በድርድሩም በአምስት መጠነኛ ቴክኒካዊ ጉዳዮችና በሶስት ዋና የህግ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ባለመደረሱ ነው ሳይቋጭ የቀረው።
የሶስቱ አገራት ተደራዳሪ ቡድኖች በአፍሪካ ህብረት እና በአገራቱ መሪዎች ግምገማ የሚደረግበት ሪፖርት ማዘጋጀታቸውም ተገልጿል።
የተዘጋጁት ሪፖርቶች በአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር፣ የአፍሪካ ህብረት ቢሮ አባላትና በሶስቱ አገራት መሪዎች እንደሚገመገም ተጠቅሷል።
ሚኒስትሩ አያይዘውም የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ከማንም ጎረቤት አገር ውሃ ሳታገኝ ለሁሉም ትሰጣለች ብለዋል።
ይህም በመሆኑም በቀጣይ የወንዞቹን ጉዳይ በተደራጀ መልኩ መተንተንና መምራት የሚችል ተቋም አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ ካልሆነ ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር ችግር ውስጥ ስለሚከታት የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጉዳይ በልዩ ሁኔታ የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ሲካሄድ የነበረው የህዳሴ ግድብ የሶሰትዮሽ ድርድር ከተቋረጠ በኋላ ከሰኔ 5 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ድርድሩ ዳግም መቀጠሉ የሚታወስ ነው።
የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን ስምምነት ባልደረሱባቸው ጉዳዮች ላይ ተነጋግረው በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከስምምነት መድረስ እንዳለባቸው መግለጹም ይታወሳል።