ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ለማቋቋም የተሻሻለውን አዋጅ አፀደቀ

አዲስ አበባ ሀምሌ 8/2012(ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን አዋጅ አጸደቀ።


የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል።

ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባውም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ለማቋቋም የቀረበውን የተሻሻለውን አዋጅ ጨምሮ 2 የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።

ዛሬ ከፀደቁት አዋጆች መካከል የምክር ቤቱን አባላት በስፋት ያከራከረው እና ያወያየውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ለማቋቋም ተሻሽሎ የቀረበውን አዋጅ አባላቱ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።

ምክር ቤቱ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው 4ተኛ ልዩ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ የመጀመሪያ ንባብ ካካሄደ በኋላ ለዝርዝር እይታ ለህግ ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶት ነበር።

ቋሚ ኮሚቴው ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር ከተመለከተ በኋላ የምክር ቤቱ አባላት እንዲያፀድቁት የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።

በዚህ መሰረት በረቂቅ አዋጁ የምርማራ ሂደት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን እና የተለዩ ጭብጦችን ጨምሮ በአዋጁ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች ላይ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አበራ ጌዴቦ ለምክር ቤቱ አባላት ገለፃ አድርገዋል።

ሰብሳቢው ካቀረቡት ማሻሻያዎች የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በትርፍ ጊዜያቸው ሌላ ሥራ ቢሰሩ በሚል የተሻሻለው አንቀጽ በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

ኮሚሽነሮች በኮሚሽነርነት ከማገልገል በተጨማሪ የጥቅም ግጭት የማይፈጥር እስከሆነ ድረስ ለአገር በሚጠቅም መልኩ ሌላ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የሚፈቅድ ስርዓት ቢፈጠር የሚለውን ሀሳብ የምክር ቤቱ አባላት ተቃውመውታል።

በተሻሻለው አዋጅ ላይ ኮሚሽነሩ በምርጫ ወቅት በምርጫ ታዛቢነት እንዲሰራ በሚል የቀረበ ሀሳብንም በምክርቤቱ አባላት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።


በመጨረሻም ኮሚሽነሮች በትርፍ ጊዜያቸው ሌላ ሥራ ቢሰሩ የሚለው አንቀጽ እንዲወጣ በሚል ከምክር ቤቱ አባላት የቀረበ ጥያቄ በድምጽ ብልጫ አሸንፎ አዋጅ ቁጥር 1224/2012 ሆኖ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል።

ምክር ቤቱ በተመሳሳይ የማህበረሰብ ተፋሰስ ልማት፣ አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅን እንዲሁም የሜርኩሪ ንጥረነገር በሰውና አካባቢ ላይ የሚያደርስውን ችግር ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀውን የሚኒማታ ስምምነትን አዋጅ በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ አጽድቋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ምክር ቤቱ የ2012 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በማድመጥ ውይይት አድርጓል።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 58 ረቂቅ አዋጆች መጽደቃቸውንና በ12 የውሳኔ ሀሳቦች ላይ ውሳኔ መተላለፉ በሪፖርቱ ተመልክቷል።

ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ ያፀደቃቸው አዋጆቸና ውሳኔዎች በይዘትና በዓላማቸው የአገርና ህዝብ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚደግፉ እንዲሁም የህዝብ ጤንነትና ደህንነት ከማረጋገጥ አንጻር ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም