የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ አሳሰቡ።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች በሱሉልታ ወረዳ ደርባ ከተማ አካባቢ የአረንጓደ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና የተጠሪ ተቋማቱ ሠራተኞች በዚሁ ሥፍራ ከ27 ሺህ 700 በላይ ችግኖችን ተክለዋል።
በችግኝ ተካላው ወቅትም "ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን ከራሷ አልፎ ለተፋሰሱ ሀገራትም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው" ተብሏል።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ሲሆን ችግኞችን መትከል አካባቢን ከመራቆት መከላከል ባሻገር ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ዘለቄታዊ ዋስትና መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በዋናነት ለራሷ ነው የምትሰራው ያሉት ሚኒስትሩ በተጨማሪም የተፋሰሱ ሀገራት ውኃ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ሥራ የአፈር መሸርሸርን ስለሚያስቀር የተፋሰሱ ሀገራት ፕሮጀክቶችም በደለል እንዳይሞሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብረሃ አዱኛ በበኩላቸው የሕዳሴ ግድቡ የሁሉም አሻራ ያረፈበት በመሆኑ ከወዲሁ ልንከባከበው ይገባል ብለዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራ መሥራታችን የሕዳሴ ግድቡ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጠን ማስቻልም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ እንዳሉትም እየተለወጠ የመጣውን የዓለማችንን የአየር ጠባይ ለማስተካከል የአካባቢ ጥበቃ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብ እንዲጸድቁ ማድረግም ይገባል ብለዋል።
የብሔራዊ ሚትሮዎሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክትር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው እየተለወጠ የመጣውን የአየር ጠባይ ለማስተካከል ችግኝ መትክል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት በ115 የችግኝ ጣቢያዎች ከ100 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ያዘጋጁ ሲሆን ሁሉም በዚህ ዓመት ይተከላሉ ተብሏል።