በድሬዳዋ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የክልሎች ከ20 ዓመት በታች የቼዝ ሻምፒዮና ውድድር ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የክልሎች ከ20 ዓመት በታች የቼዝ ሻምፒዮና ውድድር ተጠናቀቀ
ድሬዳዋ ሀምሌ 2/2010 በድሬዳዋ ለአንድ ሳምንት ሲካሄድ የቆየው የክልሎች ከ20 ዓመት በታች የቼዝ ሻምፒዮና ውድድር በቡድን የትግራይ ክልል አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ድሬዳዋና አማራ በግል የተካሄደውን በአሸናፊነት አጠናቀው የዋንጫና የወርቅ መዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ዛሬ ማምሻውን በተካሄደው የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ በበላይነት ውድድሩን ያጠናቀቁ ስፖርተኞች በቀጣይ ሀገራቸውን በስፖርቱ ብርቱ ተፎካካሪ ለማድረግ እንደሚሰሩ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቼዝ ፌደሬሽን ከድሬዳዋ አስተዳደር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ከ20 ዓመት በታች ሀገር አቀፍ የቼዝ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ድሬዳዋና አዲስ አበባን ጨምሮ የትግራይ፣ የአማራ፣ የደቡብና የኦሮሚያ ክልሎች ተካፍለዋል፡፡ ከሰኔ 25 እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2010 በተካሄደው በዚሁ ውድድር የትግራይ ቡድን በሴትና በወንድ የቡድን ውድድሮች በአንደኝነት በማጠናቀቅ የዋንጫና የወርቅ መዳሊያ ተሸላሚ በመሆን ውድድሩን በበላይነት አጠናቋል፡፡ በሴቶች የቡድን ውድድር ሁለተኛ አማራ ሶስተኛ ደግሞ ኦሮሚያ ሲሆኑ በወንዶቹ ምድብ ደግሞ ኦሮሚያ ሁለተኛ ድሬዳዋ ሶስተኛ ሆነዋል፡፡ በግል የወንዶች ውድድር የድሬዳዋ ማራኪ እንድሪያስ የበላይ ሆኖ የወርቅ መዳሊያና የዋንጫ ባለቤት ሲሆን በሴቶች የግል አሸናፊ የሆነችው የአማራ ክልል ስፖርተኛ መቅደስ አማረ ናት፡፡ በሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ የትግራይ ስፖርተኛ ክብሮም በርሔ በሰጠው አስተያየት ''ክልላችን ለስፖርቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶት በመሰራቱ ውጤታማ ሆነናል'' ብሏል፡፡ ''በቀጣይ ሀገሬን ልክ እንደአትሌቲክሱ በአለም አደባባይ የማስጠራት ዓላማዬን ለማሳካት ጠንክሬ እሰራለሁ'' ብሏል፡፡ ''ውድድሩ ችሎታዬን ይበልጥ እንዳሳይ አድርጎኛል፤ አንድ ቀን ድሬደዋንም ሆነ ሀገሬን በስፖርቱ ስማቸው እንዲነሳ አደርጋሁ'' ያለው ደግሞ በወንዶች የግል ውድድር የበላይ ሆኖ የወርቅና የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ማራኪ እንድሪያስ ነው፡፡ የአማራ ክልልን ውጤታማ ያደረገችው መቅደስ አማረ ውድድሩ ጥሩና ጠንካራ ፉክክር የታየበት እንደነበር ጠቅሳ ስፖርቱ ይበልጥ መሰረቱ እንዲጠናከር ከ20 ዓመት በታች ለሆኑት ወጣቶች ተለይቶ የተዘጋጀው ውድድር ሊበረታታ እንደሚገባ ተናግራለች፡፡ የኢትዮጵያ የቼዝ ፌደሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፉ በላይነህ ለአንድ ሳምንት ከተካሄደው የታዳጊ ወጣቶች ውድድር ለብሔራዊ ቡድን የሚመጥኑ ምርጥ ስፖርተኞች እንደተገኙበት ጠቅሰው እነዚህ ስፖርኞች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ ስፖርቱ ይበልጥ እንዲጠናከር በየዕድሜ እርከኑ በርከታ ውድድሮች እየተዘጋጁ መሆኑንና እድሜያቸው ከ13 ዓመት ጀምሮ ያሉ ወጣቶች በፕሮጀክት እንዲታቀፉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመዝጊያው ሥነ-ሥርዓት ላይ ለአሸናፊዎቹ የተዘጋውን የዋንጫ ፣ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ መዳሊያ የሸለሙት የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ከድር ጁሃርና ሌሎች እንግዶች ናቸው፡፡