የብልፅግና ፓርቲን ህገ-ደንብና ፕሮግራም ማወቃችን የፓርቲውን ዓላማ ተገንዝበን እንድንጓዝ ያደርገናል--አባላቱ

60

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2012 ( ኢዜአ) የብልፅግና ፓርቲ ህገ-ደንብና ፕሮግራም ላይ ውይይት መደረጉ የፓርቲውን ዓላማ ተገንዝበው እንዲጓዙ እንደሚያደርጋቸው የትግራይ የብልፅግና ፓርቲ አባላት ገለፁ።

"ብልፅግና ፓርቲን ተቀላቅለን በአገራዊ ልማት እንሳተፋለን" በማለት ፍላጎት ያሳዩ የትግራይ ተወላጆች በፓርቲው ህገ-ደንብና ፕሮግራም ላይ ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል።

በየካ ክፍለ ከተማ የትግራይ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት በፓርቲው ህገ-ደንብና ፕሮግራም ላይ የውይይት መድረክ አካሂደዋል።

በመድረኩ ከዚህ ቀደም የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) አመራር የነበሩ እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲን ዓላማ ደግፈው የመጡ የትግራይ ተወላጆች በፍላጎታቸው አባል ሆነው ለመቀጠል የወሰኑ የተሳተፉበት ነው።

''የብልፅግና ፓርቲ አላማና ፕሮግራም ቀድሞ ከነበረው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የተለየ በመሆኑ መድረኩ ያስፈልጋል'' ብለዋል።

በመድረኩ ተሳታፊ ከነበሩ ውስጥ አቶ ታሪኩ አድሃና እንደገለጹት፤ ኢህአዴግ ከግንባር ወደ ውህድ ፓርቲነት ከተቀየረ ጀምሮ ሦስቱ ፓርቲዎች ቀድመው ብልፅግናን ቢቀላቀሉም ህወሃት ግን ሳይቀላቀል ቀርቷል።

''የፓርቲውን ዓላማና ፕሮግራም በሚገባ ተረድተን እንድንቀሳቀስ መድረኩ ያስፈልጋል'' ያሉት ደግሞ ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ መድህን ገብረመስቀል ናቸው።

የክፍለ ከተማው የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በበኩላቸው ''መድረኩ የትግራይ ተወላጆች ባሳዩት ፍላጎት መሰረት የተዘጋጀ ነው'' ብለዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ጎሳ እንዳሉት፤ ውይይቱ 'ብልፅግና ፓርቲን ተቀላቅለን አገር መምራት እንፈልጋለን' ብለው ያሉ የትግራይ ተወላጆች ፓርቲውን አውቀው እንዲሄዱ የተደረገ ነው።


በውይይቱ ከ70 በላይ የህወሃት አባላት የነበሩ መሳተፋቸውን ገልፀው፤ በቀጣይም በርካታ የክልሉ ተወላጆች ብልፅግናን ለመቀላቀል ፍላጎት በማሳየታቸው ተመሳሳይ መድረክ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የየካ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በበኩላቸው በመድረኩ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ሌሎች ፓርቲውን መቀላቀል የሚፈልጉ የክልሉ ተወላጆች ወደ ፓርቲው እንዲመጡ የሚያስችል እንደሆነ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም