በኢትዮጵያ 1 ኪሎ ግራም ቡና በ13 ሺህ 838 ብር ተሸጠ

104

አዲስ አበባ ሰኔ 21/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ በቆየው የባለልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ አንድ ኪሎ ግራም ቡና በ13ሺህ 838 ብር መሸጡን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር  አዱኛ ደበላ  እንደጠቆሙት ፤  በውድድሩ ያሸነፈው ቡና አንድ ኪሎ በ407  የአሜሪካን  ዶላር ወይም  በ13 ሺህ 838 ብር ሊሸጥ ችሏል፡፡

ጨረታውን ያሸነፈው  'ማሩያማ' የተባለ የጃፓን ኩባንያ መሆኑን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አሸናፊው በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ክልል  ውስጥ ያሉት አርሶ አደር ንጉሴ ገመዳ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡፡

ጨረታው የተካሄደባቸው 28 ቡናዎች ደግሞ በአጠቃላይ 1 ሚሊዮን 348 ሺህ 690 ዶላር የተሸጡ ሲሆን ይህም በ'ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ' የቡና ጨረታ ውድድር ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን ጠቁመዋል።

''ውድድሩ ኢትዮጵያ የተለያየ የቡና ዝርያ  ያላት አገር መሆኗን  ለዓለም  ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤  ከ33  አገሮች  የተውጣጡ 168 ቡና ገዢዎች አንደኛ  የወጣውን ቡና  ለመጫረት  ፍላጎት ማሳየታቸውን አውስተዋል።

'ኮፊ አት ኢንተለጀንሺያ' የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ ደግሞ ከሲዳማ በሁለተኛ ደረጃ ያሸነፈውን የሩማድሮ ቡና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ቡና በፓውንድ 108 ዶላር ወይም 3 ሺህ 672 ብር እንደገዛ ገልጸዋል።

በሶስተኛ ደረጃ ከፍተኛ የጨረታ ዋጋ አግኝቶ ቡናውን የሸጠው ቴስቲ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሲሆን በፓውንድ 66 ነጥብ 6  ዶላር  ወይም 2   ሺህ 264 ብር መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ምርቱን የገዛው ደግሞ ብላክ ጎልድ ኮፊ የተሰኘ የታይዋን ኩባንያ መሆኑ ታውቋል።

ጨረታው የተካሄደባቸው 28 ቡናዎች ደግሞ በአማካይ በፓውንድ 28 ዶላር ተሽጠዋል፡፡

እነዚህ 28 ቡናዎች ደግሞ በአጠቃላይ 1 ሚሊዮን 348 ሺህ 690 ዶላር የተሸጡ ሲሆን ይህም በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ የቡና ጨረታ ውድድር ታሪክ የመጀመሪያው ነው ተብሎ ተመዝግቧል፡፡

በ'ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ' የቡና ጨረታ ውድድር ታሪክ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ሽያጭ ተብሎ የተመዘገበው የኤልሳልቫዶር ሲሆን 830 ሺህ 245 ዶላር ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም