የአረንጓዴ አሻራ ትግበራን ማረጋገጥ የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ማሰብሰቢያ ስርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ ትግበራን ማረጋገጥ የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ማሰብሰቢያ ስርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን የአረንጓዴ አሻራን ትግበራ ማረጋገጥ የሚያስችል በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ ማሰባሰቢያ ስርዓት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ቴክኖሎጂው ሙሉ የዛፉን የህይወት ታሪክ ከእቅድ ጀምሮ አድጎ አገልግሎት መስጠት እስከሚችልበት ያለውን ሂደት መከታተል የሚችል ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አህመዲን መሀመድ እንደገለጹት፤ የመረጃ ማሰባሰቢያ ስርዓቱ አንድ ሰው የተከለው ችግኝ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለመከታተል ያስችላል።
ታማኝ የሆነ የችግኝ ተከላ መረጃ እንዲኖርም የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው የሰው ልጅ በአየር ላይ የሚለቀውን በካይ ጋዝን የሚመጥን ንጹህ አየር ማመንጨት የሚችሉ ዛፎችን እንዲተክል መረጃ በመስጠት የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል።
''ይህም እያንዳንዱ ግለሰብ ከነቤተሰቡ ለአረንጓዴ አሻራ የድርሻውን መወጣት እንዲችል መነሳሳትን ከመፍጠር ባለፈ አንደ አገር የሚሰራውን ስራ ያግዛል'' ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂው ያሰባሰበው መረጃ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች መመዝገቡን ገልጸው፤ ''በቀጣይም በትግርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በሶማሌኛና በአፋርኛ ቋንቋዎች የመመዝገብ ስራ ተጀምሯል'' ብለዋል።
መረጃዎቹን 'ግሪን ሌጋሲ ኢትዮጵያ' በሚል በማህበራዊ ሚዲያና በድረ-ገጽ በዝርዝር እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
ለስራውም በተቋሙ የቴክኖሎጂ ቡድን ተቋቁሞ መረጃ ወደ ሶፍት ዌር የማስገባት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህን መረጃ የሚያቀብሉ እስከ ወረዳ መዋቅር ድረስ ያሉ ባለሙያዎች ተመድበው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው ያለፈውን ዓመት የችግኝ ተከላ መነሻ በማድረግ የተጀመረ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር አህመዲን፤ መንግስት በአረንጓዴ አሻራ እየሰራ ያለውን ስራ ዝርዝር መረጃ እንደሚይዝ ተናግረዋል።
''ችግኞችን ለመንከባከብና የሚገጥማቸውን ችግር በፍጥነት ለመፍታትና የጽድቀት መጠናቸውን ለመጨመር ድጋፍ ያደርጋል'' ነው ያሉት።
ይህ ደግሞ እንደ አገር የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ግቡን እንዲመታ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
በቴክኖሎጂው የሚሰባሰበው መረጃ ለውሳኔ ሰጪዎች፣ ለፖሊሲ አውጪዎችና ለአጥኚዎች የተሟላ መረጃ በመስጠት ረገድ ጠቃሚ እንደሚሆን አመልክተዋል።
ባለፈው አመት ክረምት ላይ በተካሄደው መርሃ ግብር በአንድ ጀምበር 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል በተያዘው ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ቀን የተካሄደው የችግኝ ተከላ በቴክኖሎጂ በመታገዝ መመዝገቡ ይታወሳል።
በዚህም በዕለቱ ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉ መረጋገጡ ይታወቃል።