የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ይሰራል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2012 (ኢዜአ) በአገሪቷ የሚስተዋለውን የዋጋ ግሽበት በዘላቂነት ለመፍታት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ ለኢዜአ እንደገለጹት የአገሪቷ የዋጋ ግሽበት የምርትና ምርታማነት አለማደግና የገበያ ስርዓቱ ውስጥ ያለው ችግር እንደሆነ አንስተዋል።
"የዋጋ ንረት አብሮን የቆየ ዳተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል" ያሉት ዶክተር ዕዮብ ይህን መፍታት የሚቻለው ግን ''አንዳንዶች እንደሚያስቡት በቁንፅል መፍትሄ አይደለም" ብለዋል።
አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች "የገንዘብ በኢኮኖሚው ውስጥ መብዛት የዋጋ ግሽበት አምጥቷል" የሚል ቁንፅል ትንተና እና መፍትሄ ያስቀምጣሉ ነው ያሉት።
የዋጋ ግሽበት ገንዘብ በኢኮኖሚ ውስጥ በሚንቀሳቀስበት መጠን ቢወሰንም ከዚሁ እኩል የአቅርቦትና የፍላጎት ጉዳይ ትልቁ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢኮኖሚው ትልቁ ችግር የምርትና ምርታማነት አለማደግ በመሆኑ ይህ ሲፈታ በአጠቃላይ የዋጋ ግሽበትን ጨምሮ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ያስተካክላል ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት አለበት ሲባል የዕዳ ጫናው፣ የዋጋ ግሽበቱ፣ ለግሉ ሴክተር ይቀርብ የነበረው ፋይናንስ ዝቅተኛ መሆንን ከሚነሱ ችግሮች መካከል ጠቅሰዋል።
"ከአገር ውስጥ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ወጪያችንን መሸፈን በሚያስችለን ረገድ ሪፎርም ማድረግ አለብን" ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።
ከውጭ የሚመጣው ብድር በዋጋ ግሽበቱ ላይ ሚና እንዳለው ቢነገርም ከ2013 ዓ.ም በጀት አንጻር እንኳ ሲታይ ከአጠቃላይ በጀቱ የተካተተው የውጭ ብድር 20 ቢሊዮን ብር አይሆንም ነው ያሉት።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት እንዲኖር የተለያዩ ሪፎርሞች ሲተገበሩ መቆየታቸውን በማንሳት የኮሮና ወረርሽኝ ሲከሰት መናጋት ያልተፈጠረውም ለዚሁ ነው ብለዋል።
በዚህ ዓመት ከተሰሩ ስራዎች መካከል ግብርናውን በመደገፍ ውጤታማ ለመሆን ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የመስኖ ስራዎች፣ የከተማ ግብርናን መደገፍ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ትርጉም እንደሚያመጡም አውስተዋል።
የመስኖ ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በርካታ የውሃ ፓምፖች በግዥ ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለአርሶ አደሮች መከፋፈላቸውንም ገልጸዋል።
እንደ ስንዴና ዘይት ያሉ ምርቶችን ለማስገባት የተለዩ አሰራሮችን በመከተል ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ባልተለመደ መልኩ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲጋብዝ ተደርጎ አቅርቦታችን ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።
በሌላ በኩል ኢንዱስትሪዎች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሠራተኞቻቸውን ሳይበትኑ ምርታማ ሆነው እንዲቆዩ መሆናቸው ኢኮኖሚው የበለጠ አንሰራርቶ እንዲቀጥል የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል።
ይህም ከፍላጎቱ ጋር ሲቀራረብ ዋጋውን በማስተካከል ረገድ የራሱ የሆነ ትልቅ አንድምታ አለው እንደ ዶክተር እዮብ ገለጻ።
ሌላው የዋጋ ግሽበት ችግር ከቤት ኪራይ ጋር የተገናኘ ሲሆን ይህንንም ለማስተካከል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኪራይ አስተዳደርና የቤት አቅርቦት ላይ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
"እነዚህ አንድ ላይ ሲመጡ በዋጋ ግሽበት በኩል ያለብንን ተግዳሮት የሚቀርፉ ይሆናሉ" ነው ያሉት።
የማክሮ፣ የፊስካልና የሞኒተሪንግ ፖሊሲ ጥብቅና የተናበቡ መሆናቸውን በማረጋገጥ እነዚህ ሲደጋገፉ የዋጋ ግሽበቱ እየተረጋጋ እንዲመጣ ያደርጋል ብለዋል።
የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች በተያዘው አቅጣጫ ሲቀጥሉ ኢኮኖሚው ጥሩ እንቅሰቃሴ ውስጥ እንደሚገባም አመላክተዋል።