ወልዲያ ዩኒቨርሲቲና ደሴ የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ወልዲያ ዩኒቨርሲቲና ደሴ የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ
ሰቆጣ/ደሴ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) የወልዲያ ዩኒቨርሲቲና በደሴ ከተማ የሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ለተቸገሩ ወገኖች የምግብ ድጋፍ አደረጉ።
የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እሸቱ ማርየ ዛሬ በሰቆጣ ከተማ ለተቸገሩ ሰዎች ድጋፍ ባደረጉበት ወቅት እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ መከሰት ዜጎችን ለችግር አጋልጧል።
በአሁኑ ወቅት ሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የዕለት ምግባቸውን መሸፈን ለማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሦስት ሚሊዮን 600 ሺህ ብር የሚገመት የምግብ እህል ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በሰቆጣ ከተማ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች 241 ሺህ ብር ግምት ያለው 70 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ ሽሮ፣ ክክና በርበሬ በድጋፍ ተሰጥቷል ብለዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ደስታ በበኩላቸው የቫይረሱን ክስተት ተከትሎ በአስተዳደሩ ከ85 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ናቸው ብለዋል።
በዚህም ዩኒቨርሲቲው ያደረገው የምግብ እህል ድጋፍ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 110 የኅብረተሰብ ክፍሎች ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።
በቀጣይም የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶችን በማስተባበር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ አልማዝ በየነ በሰጡት አስተያየት በዩኒቨርሲቲው የተሰጣቸው የምግብ እህል ዕርዳታ ችግራቸውን እንደሚያቃልላቸው ገልጸዋል።
ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ሲል በሰቆጣ ከተማ ለተቋቋመው የኮሮና ቫይረስ የሕክምና ማዕከል 112 በላይ አልጋዎችንና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉም ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደሴ ከተማ የሚገኙ የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች በኮሮና ምክንያት ለተቸገሩ 100 አቅመ ደካሞች በነፍስ ወከፍ 10 ኪሎ ግራም ዱቄት፣ ሁለት ሊትር ዘይትና ፓስታ ለግሰዋል።
ሠራተኞቹ ድጋፉን ያደረጉት ከገቢያቸው በመቀነስ ባዋጡት ገንዘብ የገዙት መሆኑንና በቀጣይ ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ማቀዳቸውን በባንኩ የደሴ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ ዓሊ ገልጸዋል።
ድጋፉን የሰጡት በደሴ ከተማ በሚገኙ የተለያዩ ቅርንጫፎች የሚሰሩ የባንኩ ሠራተኞች ናቸው ብለዋል።
የተከሰተውን የደም እጥረት ችግር ለማቃለል እሳቸውን ጨምሮ የባንኩ ሠራተኞች ደም መለገስ መጀመራቸውን አመልክተዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ሶፍያ አራጋው በሰጡት አስተያየት በበሽታው ምክንያት ተንቀሳቅሰው መሥራት ባለመቻላቸው ሲቸገሩ እንደቆዩ ገልጸው ዛሬ ያገኙት ድጋፍ ጊዚያዊ እፎይታ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።