ቀጥታ፡

ከተማ አስተዳደሩ እምቦጭን ለመከላከል የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

ሰኔ 20/2012(ኢዜአ) ለእምቦጭ መከላከል የሚውል የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ ዛሬ በባሕር ዳር አበርክተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ መልኩ ለእምቦጭ መከላከል ተግባር የሚውል የገንዘብ ድጋፍ አድርጎ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ ከተማ አስተዳደሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ከ500 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የኮሮናቫይረስ መከላከያ የፊት እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፍ የተደረገውም ከ26 ሺህ በላይ ጭምብል ነው።

ጣና የበርካታ ወንዞች መዳረሻ፣ የገዳማት መገኛ እና የብዝኃ ሕይወይ መገኛ እና የበርካቶች የኑሮ መሠረት፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሠረት መሆኑንም ኢንጂነር እንዳወቅ አንስተዋል።

ጣና በእምቦጭ አረም ወረርሽኝ መታመሙን፣ በደለል፣ በፍሳሽ እና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን በመረዳት የአዲስ አበባ ከተማ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጣናን ለመታደግ በባሕር ዳር መገኘታቸውንም አስታውቀዋል።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጣናን ለመታደግ በጉልበታቸው እና በገንዘባቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ በጎ ተግባራት በመሠማራት በርካታ ሥራዎች እያከናወኑ መሆኑን ያነሱት ኢንጂነር እንዳወቅ የዛሬው ተግባራቸው ከአማራ ክልል በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት አጋጣሚ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢንጂነር እንዳወቅ የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል ትኩረት እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የተጀመረው ድርድር በአሸናፊነት እንዲጠናቀቅ መላው ኢትዮጵያውያን ሁሉንቀፍ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶክተር) ለተደረገው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያገለግሉ ፈሳስ ሳሙናዎችን፣ የፊትና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች እና ሳኒታይዘር ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ወጣት በጎ ፈቃደኞች በባሕር ዳር ተገኝተው ድጋፉን ማስረከባቸውን አብመድ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም