ቀጥታ፡

ኅብረተሰቡ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የመረዳዳት ባህሉን እንዲያሳደግ ፕሬዘዳንቱ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) ኅብረተሰቡ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የመረዳዳት ባህሉን እንዲያሳደግ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዘዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ ጠየቁ።

በወረርሽኙ ሳቢያ ገቢያቸውን ያጡትንና ወጥተው መሥራት ያልቻሉ ዜጎችን መደገፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የሟች ወይዘሮ አልማዝ ገብረ አማኑኤል ቤተሰቦች በወረርሽኙ ምክንያት ለተጎዱ ለ180 ሰዎች ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በወረርሽኙ ሳቢያ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ከ142 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የምግብና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለግሰዋል።

ፓስተር ጻዲቁ በዚሁ ወቅር ድጋፉ በዓርአያነቱ የሚጠቀስና የተቸገሩ ወገኖችን የሚታደግ ነው ብለዋል።


ወረርሽኙ በአገራችን እንደተከሰተ የነበረው ጥንቃቄ ጥሩ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን የሚታየው መዘናጋት መቀየር ይገባዋል ብለዋል።


በበሽታው የተዘናጉ ያደጉ አገሮችን ዋጋ ያስከፈለ በመሆኑ ኅብረተሰቡ በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ እንዲያደርግ ፓስተር ጻዲቁ አሳስበዋል።

በሽታውን ለመከላከል መረዳዳትን ባህላችን ልናደርግና ዕርዳታ የሚፈልጉ ዜጎችን ልናግዝ ይገባል ብለዋል።

የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን አረጋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ባቀረቡት ጥሪ መሠረት በወረርሽኙ ሳቢያ ወጥተው ለማይሰሩና አነስተኛ ገቢያቸው ለተቋረጠባቸው የወረዳው ነዋሪዎች ድጋፉ መሰጠቱን ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያኗ ድጋፉን ስታስተባብር ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ጠቁመው፤ አሁን እየተደረገ ያለው ድጋፍ ነገ ለሌላ እንዲያደርጉት ዓርአያነትን ሁሉ ያሳየ ነው ብለዋል።

ዕርዳታ ከተደረገላቸው መካከል ወይዘሮ ሙሬዳ ጀማል በልብስ እጥበት ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ግን በወረርሽኙ ምክንያት ችግር ውስጥ እንደወደቁ ይገልጻሉ።


በድጋፉ የተገለጸውን መልካምነት እሳቸውም ለሌሎች ለማድረግ ተነሳሽነትን ፈጥሮብኛል ብለዋል።


መሪጌታ ፅጌ ለይኩን በበኩላቸው መረዳዳት ሃይማኖታዊ ሥርዓት በመሆኑ ይህንን በጎ ሠናይ ምግባር በሁሉም የእምነት ተቋማት እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም