በአዲስ አበባ ከተማ በኳስ ሜዳ አካባቢ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ደጋፊዎች ደም ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ በኳስ ሜዳ አካባቢ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ደጋፊዎች ደም ለገሱ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ የኳስ ሜዳ አካባቢ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎችና የመረዳጃ ዕድር አባላት ደም ለገሱ።
የክለቡ ደጋፊና 250 የዕድሩ አባላት የደም ልገሳውን ያደረጉት ከኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ መረዳጃ ዕድርና ከክፍለ ከተማው ወረዳ ዘጠኝ አስተዳደር ጋር በመተባበር ነው።
"የክለቡ ደጋፊዎችን ደም ለመለገስ ያነሳሳቸው ዋነኛ ምክንያት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ልገሳው መቀዛቀዙና በከተማዋ በሚከሰተው የትራፊክ አደጋ የተጎዱ ወገኖች በደም እጥረት ሕይወታቸው እንደሚያልፍ በመገንዘባቸው ነው'' ሲሉ የዕድሩ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሰብሳቢ አቶ ሚኪያስ መንገሻ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት ዕድሩ ወጣቶችን በማስተባበር ከባለሃብቶችና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ግምቱ 78 ሺህ ብር የሚገመት ምግብና ቁሳቁስ በማሰባሰብ ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
በቀጣይም አገሪቱንና ከተማዋን ለማልማት ወጣቶቹ በጉልበታቸውና በዕውቀታቸው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ የወረዳ ዘጠኝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ነገራ ወጣቶቹ በበጎ ፈቃደኝነት ያደረጉት የደም ልገሳ ለሌሎች አርአያነት ያለውና አስተማሪ ነው ብለዋል።
ልገሳው በክረምት ከሚደረገው የበጎ አድራጎት ተግባራት አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል።
ወጣቶቹ ከዚህ በፊት በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት የምግብ ቁሳቁስ በማሰባሰብ ለተቸገሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።
ይህንን በጎ ተግባራቸውን በማጠናከር በክረምት ወራት ለሚደረጉ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳትና ሌሎች በጎ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።
የብሔራዊ የደም ባንክ ነርስ አቶ የማነ እሸቱ ወጣቶች በደም እጥረት ምክንያት የዜጎች ሕይወት እንዳይጠፋ ያደረጉት በጎ ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል።
አባላቱ በቀጣይ በመደበኛነት ደም እንደሚለግሱ ቃል ገብተዋል።