ቀጥታ፡

በብልሽት ተቋርጠው የነበሩ አሸጎዳ የነፋስ ሃይል ማመንጫ ተርባይኖች አብዛኛዎቹ ስራ ጀመሩ

መቀሌ፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) በብልሽት ምክንያት ሀይል ማመንጨት አቁመው የነበሩ የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች አብዛኛዎቹ ስራ መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

በአሸጎዳ ነፋስ ኃይል ማመንጫ ከሚገኙት ተርባይኖች ውስጥ 54ቱ በብልሽት ምክንያት ስራቸው ተቋርጦ እንደ ነበር ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል  የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደተናገሩት  በተደረገላቸው ጥገና ስራ አቋርጠው ከነበሩት ውስጥ 36 ተርባይኖች  ኃይል ማመንጨት ጀምረዋል።

እነዚህን ጨምሮ አሁን በአጠቃላይ 66 ተርባይኖች ኃይል በማመንጨት ላይ  እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ቀሪዎቹ 18 ተርባይኖች ደግሞ በመለዋወጫ እቃዎች  እጥረት ምክንያት  አገልግሎት መስጠት አልቻሉም ብለዋል።

በተለይም 8 ተርባይኖቹ ብልሽቱ ከባድ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ መቀየር የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሙሉ በሙሉ ቅያሪ የሚያስፈልጋቸው ተርባይኖች ደግሞ እቃው ከተመረተበት ሀገር እንዲመጣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል  ማነጅመንት ከቦርዱ ጋር ተነጋግሮ ማስወሰኑን ጠቁመዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባስከተለው ስጋት ምክንያት  ግዥው መፈፀም ሳይቻል መቆየቱንም ተናግረዋል።

ቀላል የመለዋወጫ እቃዎች የሚፈልጉ አስር ተርባይኖች ደግሞ በአጭር ጊዜ ለማስተካከል እየተሰራ ነው ብለዋል።

የነፋስ ኃይል ማመንጪያ ለኢትዮጵያ  አዲስ ቴክኖሎጂ ቢሆንም  በተቋሙ  ሰራተኞች እውቀት እየተደረገ ያለው ጥገና  ውጤታማ እንደሆነ  አቶ ሞገስ አስረድተዋል።

የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ካሉት 84 ተርባይኖች 54ቱ  እያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 5 ሜጋ ዋት ቀሪዎቹ  ደግሞ  እያንዳንዳቸው አንድ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳላቸው ታውቋል።

የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ማመንጪያ  54 ተርባይኖች  አገልግሎት ማቆማቸውን ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም መዘገባችን ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የነፋስ ኃይል የማመንጨት አቅም ቢኖራትም እስካሁን ማመንጨት የተቻለው 320 ሜጋ ዋት ብቻ እንደሆነ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም