በነገሌ ከተማ ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በነገሌ ከተማ ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ
ነገሌ፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) በነገሌ ከተማ በኮሮና ቫይረሰ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች የምግብ እና ንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ ተደረገ።
ድጋፉን ያደረገው የጉጂ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ነው።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል አቶ ተስፋዬ ገመቹ እንደገለጹት ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖች አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኛ ሴቶች እና ህጻናት ናቸው፡፡
ድጋፉ 60 ኩንታል ስንዴ ፣ 2 ሺህ 400 ሊትር የምግብ ዘይት፣ የቤት ውስጥ መገልገያ እና ልዩ ልዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጽህፈት ቤቱ በቀጣይም ለተቸገሩ ወገኖች ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።
ማህበራዊ ርቀትን እየጠበቁ የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ እርስ በእርስ በመረዳዳትና በመተባበር የኮሮና ቫይረስ ስጋትን ለማሳለፍ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አቶ ይሳቅ ጉዮ በሰጡት አስተያየት በቀን ስራ ስድስት የቤተሰብ አባላትን እንደሚያስተዳድሩና ከበሽታው ክስተት በኋላ ስራ በመጥፋቱ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በተደረገላቸውም ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አቶ አብዲ ኑር በበኩላቸው በበሽታው ስጋት ምክንያት የነበራቸው የቀን ስራ በመገደቡ ያጋጠማቸውን ችግር ለማቃለል የተደረገላቸው ድጋፍ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።