ቀጥታ፡

አስደናቂ ተግባር የፈፀመችው ትንሿ የገጠር መንደር ልምዷን አጋራች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) በምሥራቅ ሸዋ ዞን አስደናቂ ተግባር የፈፀመችው ትንሿ የገጠር መንደር ልምዷን ለሌሎች አጋራች።

በመንደሯ የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ምክር ቤት አባላት ዛሬ የማስታወሻ ችግኞች ተክለዋል።

ቱሉ ፈራ ቀበሌ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን 157 ሰዎችን ይዞ የተከሰከሰበት ሥፍራ ናት።

በሥፍራው የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ የብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ምክር ቤት አባላት ዛሬ በቦታው የማስታወሻ ችግኞች ተክለዋል።

ሥፍራው እንደ የትኛውም የገጠር አካባቢ ያልተለየ ቢሆንም፤ ነዋሪዎቿ ግን ነፍስ ዘርተውባታል የሰው መሆን ትልቅነት አሳይተውባታል።


ለሳምንታት አንብተዋል የሚከተሉት ሃይማኖት የሚፈቀደውን ክንውን ለሟቾቹ አድርገዋል።


በወቅቱ የተፈፀመው ድርጊታቸው ብዙዎችን አስደንቋል፣ አስገርሟልም።


''ታዲያ ይህ ምን ይገርማል የሰው ልጅ ወጥቶ ሲቀር የማያዝን አለ ወይ?'' ይላል አርሶ አደር ደቻሳ መኮንን።


ባናውቃቸውም ሁሉም ሰው አንድ ነው ፤የዉጪዎቹም ቢሆኑ፤ ተምረው ማዳበሪያ ሰርተዋል ለምርታችን። ሁሉም ሰው የራሱ ነገር አለው ይላል አክሎ።


የመንደሯ ሰዎች ሌላው ሕዝብ በመገናኛ ብዙሃን ከተመለከተው በላይ እጅግ አዝነው እንደነበረም ያስታውሳል።


አውሮፕላኑ ተከስክሶ ለሁለት ሰዓት ገደማ ደርቀን ቀርተን ነበር፤ የምናደርገው ጠፍቶን በጭንቀት ተውጠን ነበር ሲልም ደቻሳ ገልጾልናል።


አርሶ አደሩ እንደሚያስታውሰው በወቅቱ የፌዴራል ፖሊስ ሥፍራውን ሙሉ በሙሉ እስኪረከባቸው ለሁለት ሳምንት ሌት ተቀን ጠብቀዋል።


ሌላው ትዝታቸውን ያጫወቱን አርሶ አደር ተስፋዬ ሰንበቱ ሟቾቹ ሰዎች በመሆናቸው ከልብ አዝነናል ይላሉ።


ወደ 10 የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች አዉሮፕላኑ የተከሰከሰበት አካባቢ የሰዎች ደም የፈሰሰበትን ቦታ አርሰን አንበላም ብለው መንግሥት ካሳ እንደከፈላቸው ተናግረዋል።


አርሶ አደሮቹ ዛሬም ስለ ሁኔታው ሲያወሩ እጅግ በተሰበረ ልብ ነው።


አርሶ አደር ተስፋዬ የሰው ልጆች አንድ በመሆናቸው አብረው ሊኖሩና ሊከባበሩ ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።


በሥፍራው ችግን የተከሉ ወጣቶች ከነዚህ ልበ ቀና አርሶ አደሮች ሰው መሆን ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ትምህርት መውሰዳቸውን ይናገራሉ።


ከደቡብ ክልል የተወከለችው ወጣት ቤተልሄም አሰፋ በዚህ ታሪካዊ ቦታ በመገኘቷ መደሰቷን ትናገራለች።

የቀበሌዋ ነዋሪዎች ሰው መሆን ምን ያህል ትልቅ እንደሆነና ቦታው ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ የታየበት ነው ትላለች።


ድርጊቱ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ማስተማሪያ ስለሚሆን ሁሉም ታሪኩን ሊያውቀው ይገባልም ነው ያለችው።


ከሐረሪ ክልል የመጣው ወጣት ጅብሪል መሐመድ ''ሥፍራው ትልቅ ታሪክ የተፃፈበት ነው'' ይላል።

በመሆኑም ይህን ታሪክ በተለይ የዛሬዎቹ ወጣቶች ሊማሩበት ይገባል ብሏል።


የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወጣት አስፋው ተክሌ በበኩሉ ተግባሩ ዓለምን ያስደነቀ ነው ብሏል።


ይህ ተግባር ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ ቀድሞም የሚታወቅበትና የሚያኮራ ባህል ነው ብሏል።

ወጣቶቹ አኩሪውን ባህላችሁን ሊጋሩና ልምድ ሊወስዱ የመጡ ናቸው ሲልም ተናግሯል።

ወጣቶቹ  ችግኞቹን ከተከሉ በኋላ ለአካባቢው አርሶ አደሮች የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁስ ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም