በህጻናትና ሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት በቃ ሊባል ይገባል -ጠቅላይ አቃቤ ህግ

84

ሰኔ 19 /2012 (ኢዜአ) በህጻናትና ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን በቃ ሊባል ይገባል ሲል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጥሪውን አቀረበ።

ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በዓለማችን ብሎም በአገራችን የኮሮና ቫይረስ ተግዳሮት እየተፈታተነን ባለበት ወቅት በህጻናትና በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ያለው መግለጫው፤ በተለይ የህግና የፍትህ አካላት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አውስቷል።

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል

በህጻናትና ሴቶች ላይ የሚፈጸመዉ ጥቃት አሰመልክቶ

ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጠ መግለጫ

በህጻናትና ሴቶች ላይ የሚፈጸመዉ ጥቃት ይብቃ የምንልበት ጊዜው አሁን ነዉ።

ዛሬ ዓለማችን ብሎም ሀገራችንን የኮሮና ቫይረስ ተግዳሮት እየተፈታተነን ባለበት ወቅት በህጻናትና በሴቶች ላይ የሚደረሰው ጥቃት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ የገሀድ ነዉ፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የህግና የፍትህ አካላት የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ጥረታቸውን ቀጥላል ፡፡

ለአብነት ባለፉት 3 ወራት ዉስጥ በአስገደዶ መድፈር በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ክስ ከተመሰረተባቸው 40 መዝገቦች፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተግዳሮት ውስጥ ሆነንም ቢሆን እስከ አሁን ድረስ 8 መዝገቦች ላይ ዉሳኔ ተሰጥቶባቸዋል።

ከእነዚህ ዉስጥ በዐቃቤ ሕግ ክስ የተመሰረተባቸው የ64 ዓመቱ ተከሳሽ በአዲስ አበባ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዕድሜያቸው ስምንት እና ዘጠኝ አመት የሆኑ ሁለት ሴት ህፃናቶችን በተለያዩ ቀናቶች ተከራይቶ ከሚኖርበት ቤት ውስጥ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽሞባቸዋል፡፡ በዚህም ተከሳሹ የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 627(1) ተላልፎ በመገኘቱ አራት ክሶችን ተመስርቶበታል፡፡

ጉዳዩ በፍጥነት ወሳኔ እንዲያገኝ በተደረገው እንቅስቃሴ ተከሳሽ የተከሰሰበትን ክስ ሊያስተባብል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ተከሳሽን በአራቱም ክሶች ጥፋተኛ ነህ ብሎታል፡፡

በዚህም ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት በ60 አመት እንዲቀጣ የፈረደበት ቢሆንም የተከሰሰበት ድንጋጌ ጣሪያው 25 ዓመት በመሆኑ በ 25 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ ከህፃንነቷ ጀምሮ ያሳደጋትን የ15 ዓመት የእንጀራ ልጁን የደፈረው ግለሰብ በ11 ዓመት ከ9 ወር ጽኑ እስራት የተቀጡ ሲሆን ቅጣታቸዉም በቂ አይደለም ተብሎ በታመነበት ላይ የይግባኝ ክርክራችን ቀጥላል። ይህ ለአብነት ተገለጸ እንጂ በሌሎች የጥቃት ፈጻሚዎች ላይ ተገቢ የህግ ቅጣት እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ከምንጊዜም በላይ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ሰለሆነም በሴቶችና ህፃናት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ህብረተሰቡ ተጋላጭ እንዲሆን ጥንቃቄ እንዲያደርግና ድርጊቱ ተፈፅሞ ሲያገኝም ከመቼውም በበለጥ ከፍትህ አካላት ጎን በመሆንና ይህን አሳፋሪና አሰነዋሪ ወንጀል በማጋለጥ እና ድርጊቱን ባለመተባበር እንዲሁም ለተጎጂዎቹ ምስክር በመሆን የህግ የበላይነት እና ፍትህ እንዲሰፍን የበኩላችን እንድንወጣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናቀረባለን።

ኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም