የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ መነሻ ሰነድ ለሕዝብ ውይይት ሊቀርብ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ መነሻ ሰነድ ለሕዝብ ውይይት ሊቀርብ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ መነሻ ሰነድ ለሕዝብ ውይይት እንደሚቀርብ የፕላንና ልማት ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የመነሻ ሰነዱ ውይይት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለ11 ቀናት ይካሄዳል።
የውይይቱ ዓላማ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በዕቅድ ዝግጅቱ እንዲሳተፉ ማስቻል፣ ከኅብረተሰቡ በሚገኝ ግብዓት ዕቅዱን ማዳበርና ግልጽ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መስጠት መሆኑን ጠቁሟል።
የተቋማት የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ መነሻ ሰነድ በሃላፊዎቻቸው በተሰጣቸው የጊዜ ሰሌዳ ለውይይት እንደሚቀርብም ተገልጿል።
ዝግጅቱ በተቋሙ የፌስ ቡክ ገጽ፣ በዩቲዩብ ቻናልና በፋና ቴሌቪዥን በቀጥታ ለሕዝብ ይቀርባል።
በውይይቱ ሠዓትም ግብዓቶችና ጥያቄዎች በኢ-ሜይል አድራሻ /contact@pdc.gov.et/ ከሕዝብ የሚሰበሰቡ ሲሆን ለጥያቄዎች ማብራሪያ ይሰጣል ነው የተባለው።
መነሻ ሰነዱ የዘርፍ መስሪያ ቤቶችና ፈጻሚ አካላት በአዘጋጅነት የተሳተፉበትና ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል።
በቅርቡም በኮቪድ-19 ተጽዕኖ ማስተካከያ እንደተደረገበት ታውቋል።
የዕቅድ ዝግጅቱ የአሳታፊነት ደረጃ፣ አዳዲስ የትኩረት መስኮችን ማካተቱ፣ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ላይ ማተኮሩ የረጅም ጊዜ ዕቅድ መሆኑ ከቀደሙት አገራዊ ዕቅዶች ልዩ ያደርገዋል ተብሏል።
ዕቅዱ ዜጎች የራሳቸው ዕቅድ መሆኑን አውቀው እንደሚያዳብሩትና ለአፈጻጸሙ የራሳቸውን አሻራ እንደሚያኖሩም ይጠበቃል ሲል የኮሚሽኑ መግለጫ አትቷል።