ቀጥታ፡

ኪነ-ጥበብ አገር በችግርና ፈተና ውስጥ ስትሆን ብርሃንና ተስፋን የማሳየት ኃላፊነቷን ልትወጣ ይገባታል

አዲስ አበባ ሰኔ 19/2012(ኢዜአ) ኪነ-ጥበብ አገር በችግርና ፈተና ውስጥ ስትሆን ብርሃንና ተስፋን የማሳየት ኃላፊነቷን መወጣት እንደሚገባት ተገለጸ። 

ኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝና እያስከተለ ያለው ጉዳት፣ የፖለቲካ አለመግባባቶች፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች፣ የጸጥታ ሁኔታ፣ ሌሎች ችግሮችና ፈተናዎች ከፊቷ ተጋርጠውባታል።

አሁን ያሉትን ፈተናዎች ለመሻገር ኪነ-ጥበብ ምን አይነት ሚና ሊኖራት ይገባል? በሚል ኢዜአ የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።

ድምጻዊ ፀደኒያ ገብረማርቆስ ኪነ-ጥበብ በእንደዚህ አይነት የችግር ወቅት ህብረተሰቡ ልብ ውስጥ ተስፋን የሚፈነጥቁ መልዕክቶች በቀላሉ እንዲደርሱ ያላት ሚና ወሳኝ እንደሆነ ገልጻለች።

ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ችግር ውስጥ በምትገባበት ወቅት ችግሩ እንዲፈታ የግንባር ቀደምትነቱን ሚና ከሚወጡት አካላት መካከል የኪነ-ጥበቡ ማህበረሰብ ዋነኛው እንደሆነ አመልክታለች።

ኪነ-ጥበብ ሌሎች ያልቻሉትን ለህብረተሰቡ የሚስቡ ነገሮችን ተደራሽ የማድረግ ከፍተኛ አቅም እንዳላትም ፀደኒያ ተናግራለች።

በአሁኑ ወቅት ኪነ-ጥበብ በጨለማ ውስጥ ብርሃን የማብራት ኃላፊነት እንዳለባት ገልጻ፤ ''ከዚህም አኳያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና አገራዊ ፈተናዎችን አስመልክቶ፣ የሙዚቃ ሥራዎች ለህብረተሰቡ እየቀረቡ ነው'' ብላለች።

የሙዚቃ ሥራዎቹ መልዕክት ህዝብ ለአገሩ በጋራ ከቆመ የማይታለፍ ችግር እንደሌለ የሚያመላክትና፣ የዜማዎቹ ግጥም ሐሳቦች ለዜጎች ብርታትን የሚሰጡ እንደሆኑ ነው ድምጻዊት ፀደኒያ የገለጸችው።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻር የኪነ-ጥበቡ ማህበረሰብ የሚኖረው አስተዋጽኦ ጉልህ እንደሆነና ዘርፉ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባው ተናግራለች።

ከታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋራ በተያያዘም የኪነ-ጥበቡ ማህበረሰብ ዜጎችን የሚያሳትፉና የሚያነቃቁ    ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝና ይህም ሊቀጥል የሚገባው ተግባር እንደሆነ ገልጻለች።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያደርሰው ጉዳት ከባድ በመሆኑ የኪነ-ጥበብ ማህበረሰቡና ዜጎች አቅማቸው የፈቀደውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቁማለች።

ተዋናይት መቅደስ ጸጋዬ በበኩሏ ''ኪነ-ጥበብ ሰዎች ችግርን አልፈው ነገን እንዲያዩና ተስፋን እንዲሰንቁ የማድረግ ጥበባዊ ኃይል አላት'' ብላለች።

ከዚህም አኳያ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከኮቪድ-19 ወረርሽኝና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ መልዕክቶችን እያስተላለፉ እንደሚገኙ ገልጻለች።

ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘም አቅም በፈቀደ መጠን ለህብረተሰቡ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግራለች።

ይሁንና በወረርሽኙ ምክንያት ከባድ ተጽዕኖ ከደረሰባቸው ዘርፎች መካከል ኪነ-ጥበብ አንዱ እንደሆነና ባለሙያዎች አሳሳቢ ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ መግባታቸውን አመልክታለች።

በችግር ጊዜ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች አገራዊ ጥሪ ቀርቦላቸውም ሆነ ሳይቀርብላቸው ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳሉ ነው የፊልም ተዋናይት መቅደስ የገለጸችው።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ከአራት ሰው በላይ መሰብሰብ የማይቻል በመሆኑ ምንም አይነት የኪነ-ጥበብ ሥራ ማከናወን ባለመቻሉ ባለሙያዎች ችግር ውስጥ እንደገቡ አመልክታለች።

እንደ ሌሎቹ መስኮች ሁሉ ለኪነ-ጥበብ ዘርፉም አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግም ጥሪ አቅርባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም