ምክር ቤቱ በ2013 በጀት ዓመት የበጀት ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በበጀት ፍትሃዊነትና አተገባበር ላይ መከረ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ በ2013 በጀት ዓመት የበጀት ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በበጀት ፍትሃዊነትና አተገባበር ላይ መከረ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2013 በጀት ዓመት የበጀት ረቂቅ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ሃሳብ ወስዷል።
በአመቱ እንዲያዝ በተዘጋጀው የበጀት ረቂቅ ከባለድርሻ አካላት ጥያቄዎችና ሃሳቦች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
በአጠቃይ ለአገሪቷ በ2013 በጀት ዓመት ከተያዘው 476 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት ውስጥ ለፌዴራል መንግስት መደበኛና ካፒታል ወጪ 293 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር፣ ለክልሎች ድጋፍ 176 ነጥብ 4 እንዲሁም ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የሚውል 6 ቢሊዮን ብር ተደግፎ ቀርቧል።
የምክር ቤቱ የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝና በሚኒስቴሩ የበጀት ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ደመቀ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች 'የቀረበው የበጀት ረቂቅ የፍትሃዊነት ችግሮች ይስተዋልበታል' በሚል ጠይቀዋል።
'የሲዳማ ክልል በጀት፣ የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችና የኢንዱስትሪያል ፓርክ ግንባታ ጥያቄ በበጀቱ ለምን አልተካተቱም' የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
በሌላ በኩል፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የምርጫ ቦርድ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ ቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተያዘላቸው በጀት በቂ እንዳልሆነ አንስተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ''የክልሎችን ድጋፍ አስመልክቶ የሲዳማ ክልል ከተዋቀረ በኋላ የክልሉ ምክር ቤት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ ልኳል'' ብለዋል።
በግልባጭ የክልሉ ጥያቄ የደረሰው የገንዘብ ሚኒስቴርም በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ ገልጸዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴርን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት መልስ በመከላከያ አዲስ አደረጃጀት መሰረት የበጀት ድልድል መደረጉን ተናግረዋል።
የምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ከተያዘለት በጀት ላይ 300 ሚሊዮን ብር በመጨመር 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተያዘለት ገልጸዋል።
''የበጀቱ መጨመር በትክክል አስፈላጊ መሆኑ ተጣርቶ ከደረሰን አስፈላጊውን እናደርጋለን'' ብለዋል።
የበጀት ድልድል ፍትሃዊትና የፕሮጀክቶች ክትትል ሂደትን በተመለከተ ለተነሳ ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል።
ዶክተር ኢዮብ እንደገለጹት፤ የፕሮጀክት አስተዳደር ላይ ችግሮች እንዳሉ ተለይቶ በዚህ አመት የበጀት ክትትል ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ ከበጀት ቁጥጥር በተጨማሪ ፕሮጀክቶችን በአካል በመገኘት እየገመገመ ነው።
በገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ደመቀ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ ''ስለ ቱሪዝም ኢትዮጵያ የተነሳው የበጀት ጥያቄ ተቋሙ ባለበጀት መስሪያ ቤት ሳይሆን መንግስት እንዲቋቋም ሲል ድጋፍ ያደረገለት ነው'' ብለዋል።
በቀጣይም የራሱን ገቢ የማመንጨት ስራ እንዲሰራ ሃላፊነት የተሰጠው መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም በተመሳሳይ በራሱ ገቢ የሚተዳደር መሆኑን ገልጸው፤ በ2013 በጀት አመት 192 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ተናግረዋል።
''ከዚህ ውጪ ግን ተልዕኮውን በሚፈታተን መልኩ የበጀት እጥረት ከተከሰተ ግን የሚታይ ይሆናል'' ነው ያሉት።
የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ በጀት ከሚያስፈልጋቸው ፕሮጀክቶች አንዱ የመንገድ ግንባታ መሆኑን ገልጸዋል።
''በበጀት አመቱም ወደ 58 ቢሊዮን ብር ከአጠቃላይ ከፌዴራል መንግስቱ በጀት 20 በመቶ የተመደበው ለዚሁ ሲሆን ይህም ክልሎችን ጭምር በአዳዲስ ፕሮጀክቶች የሚያካትት ነው'' ብለዋል።
ከወሰን፣ ከካሳ ክፍያና ከአቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች በአስፈጻሚ አካል ችግሮቻቸው ከተለዩ በኋላ ፕሮጀክቶቹን የማስቀጠል ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የአዳዲስ ዩኒቨርሲቲ ግንባታዎችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ እስካሁን በአገሪቷ 44 ዩኒቨርሲቲዎች መገንባታቸውን አስታውሰዋል።
አሁን ላይ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ከመገንባት ይልቅ ያሉትን የእውቅትና የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
''ጥራት ያለው የመማር ማስተማር ስርዓት እንዲገነቡና የምርምር ማዕከል እንዲሆኑ ጭምር የማጠናከር እንጂ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲ ለመገንባት የተያዘ በጀት የለም'' ብለዋል።
ሌሎች ተያያዥ የልማት ጥያቄዎችን በተመለከተም መንግስት የበጀት አቅሙ በሚፈቅደው መጠን ፍትሃዊ የሆነ የበጀት ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ ጥረት መደረጉን አንስተዋል።
'የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ምን ታስቧል?' በሚለው ጥያቄ ላይ በተሰጠ ምላሽ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጿል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለጥያቄዎቹ በቀረቡት ሃሳቦች ማጠቃለያ ላይ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ የበጀት ፍላጎቱና አቅርቦት ያልተመጣጠነ መሆኑን አንስቷል።