ቀጥታ፡

የጥሬ ገንዘብ ገደቡ ጤናማ የዝውውር ስርዓት እንዲኖር የማድረግ ጉልህ ድርሻ አለው - ባንኮች

አዲስ አበባ ሰኔ 19/2012(ኢዜአ) መንግስት በቅርቡ ያወጣው የጥሬ ገንዘብ ገደብ ጤናማ የዝውውር ስርዓት እንዲኖር በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ባንኮች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካለፈው ግንቦት ጀምሮ ከባንኮች የሚወጣ ጥሬ ገንዘብን የሚገድብ መመሪያ  ተግባራዊ ማደረጉ ይታወቃል።

መመሪያው ለግለሰብ በቀን እስከ 200 ሺህ ብር እና በወር ደግሞ እስከ 1 ሚሊዮን ብር፤ ለኩባንያዎች ደግሞ በቀን እስከ 300 ሺህ ብር እና በወር እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ማውጣት የሚያስችል ነው።

በሁሉም ባንኮችና አነስተኛና ጥቃቅን የፋይናንስ ተቋማት የሚተገበረው ይህ መመሪያ የገንዘብ ዝውውርን ሥርዓት በማስያዝ ወንጀልና የግብር ስወራን በመከላከል ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ታምኖበታል።

ታዲያ ይህ የጥሬ ገንዘብ ገደብ ለባንኮች ያለው ፋይዳ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሊያሳድር የሚችለው ተጽዕኖ ምን ይመስላል? ሲል ኢዜአ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የዳሸን ባንክ የስራ ሃላፊዎችን አነጋግሯል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ወጋየሁ ገብረማርያም እና የዳሽን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው አለሙ ጥሬ ገንዘብን ከማተም እስከ ማሰራጨት ባለው ሂደት ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ገንዘቦችን ለማስወገድ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ።

መመሪያው ይህን ወጪ በመቀነስና በጥሬ ገንዘብ አጠቃቀም ላይ የሚፈጠረውን ስርቆትም በመከላከል ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።

የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በመገደብ ወደ ባንኮች የሚመጣውን የገንዘብ ቁጠባ መጠን በማሳደግና ያንንም ወደ ኢንቨስትመንት በማሳደግ ለባንኮች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ትልቅ ጥቅም አለውም ብለዋል።    

በአነስተኛ ጥሬ ገንዘብ የሚንቀሳቀስ ኢኮኖሚ በሚኖርበት ጊዜም የፋይናንስ ስርዓቱን ለመቆጣጠርና ለመከታተል ይረዳል ነው ያሉት ሃላፊዎቹ።

በተቋማት ከክፍያ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት የተመቻቸ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ወጋየሁ ገብረማርያም፡-

የዳሽን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው አለሙ፡-

በሌላ በኩል ገደቡ በኅብረተሰቡ ላይ ያለውን በጥሬ ገንዘብ የመተማመንና ከአሰራሩ ለመውጣት ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆን እክል መፍጠሩን አቶ ወጋየሁ ጠቁመዋል።

በርካታ ተቋማት ክፍያ ሲቀበሉና ሲፈጽሙ ጥሬ ገንዘብን መሰረት አድርገው የሚሰሩ ከመሆኑ አኳያ ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ ለማስቻል የሚደረገው ሂደትም ሌላው ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል።

በደንበኞች በኩልም ከጥሬ ገንዘብ ውጭ ያሉ አማራጭ አገልግሎቶችን ለመጠቀም ያለው ዝግጁነት አናሳ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የዳሽን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው አለሙም ይህን ብለዋል።

መመሪያው ከተገደበው ጥሬ ገንዘብ በላይ ለሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ከአካውንት ወደ አካውንት፣ በቼክ ወይንም ደግሞ በሲፒኦ ተጨማሪ ገንዘብ ማዘዋወር እንደሚችሉም ይፈቅዳል።

በልዩ ሁኔታ መታየት ያለባቸውን ክፍያዎች በሚመለከት ለባንኮቹ ስልጣን እንደተሰጠና ወስነው ክፍያ ሲፈጸም በየሳምንቱ ለብሄራዊ ባንክ በሚያቀርቡት ሪፖርትና ክትትል የሚያልፍ መሆኑም ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም