ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ያሉ ሰዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ልዩ ትኩረት ያሻዋል - ኢዜአ አማርኛ
ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ያሉ ሰዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ልዩ ትኩረት ያሻዋል
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ።
ኮሚሽኑ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በሚመለከት ከግንቦት 12 እስከ 17 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተመረጡ ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች ፈጣን የመስክ ምልከታና ክትትል ማከናወኑን ገልጿል።
የእስረኞች ቁጥር መቀነስን ጨምሮ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማቅረብ በማረሚያ ቤት ወይም በፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ እስረኞችን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠርና ጉዳቱን ለመቀነስ መንግስት ለወሰዳቸው እርምጃዎች እውቅና እንደሚሰጥም አስታውቋል።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መርሆዎችና ደረጃዎች አንፃር አሁንም አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ስጋቶች መኖራቸውን ጠቁሟል።
ከእነዚህም በማረሚያ ቤቶችም ሆነ በፖሊስ ጣቢያዎች የነበረው መጨናነቅ በተወሰነ መጠን ቢቃለልም፤ አሁንም የእስረኞች ብዛትና የቦታው አለመመጣጠን ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት አስጊ መሆኑን መመልከቱ ይገኝበታል።
ኮሚሽኑ በአስቸኳይ ሊተገበሩ ይገባል ያላቸውን ምክረ ሀሳቦች በማከል የክትትል ሪፖርቱን ለሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል መንግስት አካላትና እገዛ ማድረግ ለሚችሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መላኩን አስታውቋል።
በሪፖርቱ እንደተመለከተው በወረርሽኙ ወቅት በእስር ላይ ያሉ ሰዎች በራሳቸው ውሳኔ አካላዊ ርቀትን የመጠበቅና በጤና ባለሙያዎች የሚመከሩ የንፅህናና የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን የማግኘት ዕድላቸው ውስን መሆኑን አንስቷል።
በመሆኑም መንግስት ካለበት በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን የመጠበቅ ሀላፊነት አንፃር ተገቢውንና ተከታታይ እርምጃ ያለማቋረጥ በመውሰድ እስረኞች ከበሽታው የሚጠበቁበትና በሕይወት የመኖር መብታቸው የሚከበርበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅበታል ብሏል።
ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በቀለ "መንግስት ብዙ አበረታች እርምጃዎች የወሰደና ብዙ እስረኞች የተለቀቁ ቢሆንም፤ እስር ቤቶች አሁንም የተጨናነቁ ስለሆነ ተጨማሪ እስረኞችን እንደ አግባብነቱ በምሕረት ወይም በዋስትና በመልቀቅ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድና የዋስትና መብትን ማረጋገጥ ይሻል" ብለዋል።
በሁሉም ክልሎች በኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች አማካኝነት ተመሳሳይ ፈጣን ክትትል እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
የሚመለከታቸው አካላት የተቋማቸውን ሁኔታ በፈጣን ክትትል ሪፖርት ከተለዩ ሁኔታዎች አንጻር በመገምገም መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና የማስተካከያ እርምጃዎች በመውሰድ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች በተሟላ መልኩ እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩም ጥሪ አቅርበዋል።